ኢትዮጵያ ለትምህርት ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት በአፍሪካ የተሻለ ልምድ የሚወሰድበት ነው-የኡጋንዳ የትምህርት ፖሊሲ ክለሳ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ

139

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለትምህርት ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት በአፍሪካ የተሻለ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን የኡጋንዳ የትምህርት ፖሊሲ ክለሳ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ  ጆሴፍ ሙቫዋላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚያከናውናቸው ስራዎች ላይ ያለውን ልምድ ለኡጋንዳ የትምህርት ጉዳዮች ልዑክ ቡድን አካፍሏል፡፡

ልዑክ ቡድኑ ዘጠኝ አባላትን ያካተተ ሲሆን፤ በኡጋንዳ መንግስት ጥያቄ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ልምድ ለመውሰድ መምጣቱም ነው የተገለጸው፡፡

በዛሬው እለትም  ከትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡


 

የኡጋንዳ የትምህርት ፖሊሲ ክለሳ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ ጆሴፍ ሙቫዋላ (ዶ/ር) ፤ ኢትዮጵያ ለትምህርት ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ልዑክ ቡድኑ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ካለው ስራ ተሞክሮ ለመውሰድ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩም በኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ እና ባለፉት ዓመታት በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በሚመለከት  ገለጻ ተደርጓል፡፡


 

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ኮራ ጡሽኔ በዚሁ ወቅት ፤ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ለጥራትና ተደራሽነት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ከተደራሽነት አኳያ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ለአብነትም የግሉን ጨምሮ ከ400 በላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡

ፖሊሲው ለተግባር ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ፣ ቴክኖሎጂን ያማከለ፤ ዘመናዊ የፈተና አሰጣጥ ስርዓተን የሚከተል እንዲሁም  ለስነ ምግባርና ግብረ ገብነትን ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም