መንግስት የዜጎችን የመጠጥ ውሃና የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከልማት አጋሮች ጋር የጀመራቸውን ትብብሮች አጠናክሮ ይቀጥላል- ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የዜጎችን የመጠጥ ውሃና የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከልማት አጋሮች ጋር የጀመራቸውን ትብብሮች አጠናክሮ ይቀጥላል- ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ መንግስት የዜጎችን የመጠጥ ውሃ እና የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከልማት አጋሮች ጋር የጀመራቸውን ትብብሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የልማት አጋር ድርጅቶች በዘርፉ እያበረከቱ ያለውን ሚናና የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ስራ ለመስራት ያለመ የባለድርሻ አካላት ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው።
መንግስት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን የውሃና የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ባከናወናቸው ተግባራት ለውጦች መምጣታቸውን ጠቅሰው፥ ካለው ፍላጎት አንጻር ግን በቂ አይደለም ብለዋል።
ይህንንም ፍላጎት ለማሟላት መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ የገጠር ኃይልና የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዛሬው ውይይትም ባለፉት ጊዜያት በትብብር በተሰሩ ስራዎች ጥሩ ጅምር መኖሩን በመገምገም በቀጣይ ትብብሩን አጠናክሮ ለመቀጠል መግባባት የተፈጠረበት ነው ብለዋል።
በተለይም ከልማት አጋሮች ለንጹህ መጠጥ ውሃና ለኃይል ተደራሽነት የሚገኘውን ፈንድ በተገቢው ስራ ላይ በማዋል ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ ነው ያነሱት።
ከዚህም ባሻገር በዘርፉ ላይ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ የተለያዩ አጋር የልማት ድርጅቶች መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የወተር ኤይድ የኢትዮጵያ ተጠሪ ያዕቆብ መተና፥ በኢትዮጵያ በውሃ እና ኢነርጂ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።
የአይ አር ሲ ወሽ የኢትዮጵያ ተጠሪ ለሜሳ መኮንታ በበኩላቸው በውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ ውጤት ለማምጣት ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል።