ቀጥታ፡

የታክስ አስተዳደር ዲጂታላይዜሽን የታክስ ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፡- የታክስ አስተዳደር ዲጂታላይዜሽን የታክስ ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚያስችል መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ። 

የገቢዎች ሚኒስቴር እና ዓለም ባንክ በጋራ ያዘጋጁት የዲጂታል ታክስ አስተዳደር ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በኮንፍረንሱ ናይጄሪያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ኡጋንዳ፣ ማላዊ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሩዋንዳ ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ሀገራት በታክስ አስተዳደር ዲጂታላይዜሽን ላይ መነጋገር፣ መፈተሽ እና ምርጥ ተሞክሮን መለዋወጥ እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

የታክስ አስተዳደር ዲጂታላይዜሽን የታክስ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና የወረቀት አሰራሮችን ለመቀየር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤መረጃዎችን የመለዋወጥ መንገድን እንደሚያሳልጠም ተናግረዋል፡፡

ይህ የሚሆነው ዲጂታላይዜሽን ላይ መስራት ሲቻል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ‘ኤሌክትሮኒክስ ኢንቮይስን’ ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገባም የተሻለ ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

የናይጀሪያ፣ ማላዊ፣ የኡጋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉሙሩክ የሥራ ሃላፊዎች የየሀገራቸውን የዲጂታል የታክስ አስተዳደር እና ሌሎች የአሰራር ተሞክሮዎችን ማቅረባቸው ተገልጿል።

በጉባኤው የገቢ አስተዳደር ዲጅታላይዜሽን፣ የገቢ ክፍል አመራር ሚና፣ የሳይበር ደህንነት ማሻሻያዎች፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ቅደም ተከተል እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እንደተካሄደባቸው ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም