ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል- ኮሚሽኑ

121

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ  ለተከሰቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት 11 ነጥብ 5  ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከውድመት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የእሳት ቃጠሎ፣ በግንባታ ወቅት የሚከሰት አደጋ፣ የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ በመዲናዋ ተደጋግመው ከሚከሰቱ አደጋዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ እና አካባቢዋ 392 አደጋዎች አጋጥመዉ 670 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ተናግረዋል፡፡

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ፈጣን የአደጋ መቆጣጠር ርብርብ 11 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል ብለዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች 39 ሰዎችን ከእሳት አደጋ፤ 85 ሰዎችን ደግሞ ከሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች በድምሩ 124 ሰዎችን በህይወት ማትረፍ እንደቻሉም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኮንስትራክሽን ፣ ተቆፍረው ክፍት በተቀመጡ ጉድጓዶች ምክንያት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዘጠኝ ወራት የደረሱ አደጋዎች ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የንብረት ውድመት መጠን በ37 ሚሊየን ብር መቀነሱን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን የመከላከልና መቆጣጠር ስራን የበለጠ እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም