የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሚያስችሉ ዲጂታል አሰራሮች በስፋት ተግባራዊ እንዲደረጉ አሳሰበ

163

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሚያስችሉ ዲጂታል አሰራሮችን ይበልጥ ተደራሽ እንዲያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንገድ ደህንነትና ፈንድ አገልግሎት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም የገፅ ለገፅ ግምገማ አካሂዷል።

ቋሚ ኮሚቴው አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ለተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ ማሰርን ጨምሮ ተሽከርካሪዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ሰራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የአሽከርካሪ ሙያ ስልጠናና ተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ የሚሰጡ ተቋማት ላይ ያለው አሰራር በዲጂታል ስርዓት የታገዘ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አሳስቧል።

የትራፊክ አደጋ በተደጋጋሚ የሚደርስባቸው ቦታዎችን በመለየት አደጋን ለመከላከል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተገለፀው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ፤ መረጃ በተገቢው መልኩ መሰብሰቡ የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና አስፈላጊ ህጎችን ለመተግበር የሚያስችል በመሆኑ  አገልግሎቱ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን እንዲያዘምን አስገንዝበዋል፡፡

ተቋሙ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ዙሪያ ያካሄዳቸው የንቅናቄና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በትምህርት ቤቶች ባሉ ክበባት ተማሪዎች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየተሰራ ያለው ስራም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አባሶ በበኩላቸው አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እያከናወነ ካለው ስራ በተጨማሪ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እየተገበረ ነው ብለዋል። 

የተለያዩ ህግና ደንብ፣ ስታንዳርዶችንና መመሪያ ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲጂታል አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ ላይም ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማትና የፍጥነት መገደቢያ አገጣጠምና አገልግሎቱን ከማዕከል ለመከታተል የሚያስችል ሶፍትዌር እየለማ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ዘመቻ በማድረግ በተሽከርካሪና አሽከርካሪዎቸ ላይ ቁጥጥርና ክትትል መደረጉንም ተናግረዋል።

በድግግሞሽ ከ9 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ በመደበኛ፣ ድንገተኛና የቴክኒክ ቁጥጥር መደረጉን ጠቅሰው፤ ጉድለት በተገኘባቸው 2 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ ቅጣት መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት በትራፊክ አደጋ የተመዘገበው ሞት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ514 መቀነሱን ተናግረዋል።

የአካል ጉዳት ደግሞ በ216 መቀነሱን ጠቁመዋል፡፡

ከመንጃ ፍቃድ አሰጣጥና ተሽከርካሪ ምርመራ ጋር የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የተሽከርካሪ ምርመራን በኦንላይን መከታተል የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የአገልግሎቱ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ፈቲያ ደድገባ ናቸው። 

የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡን ለማዘመን ከሰነድ ክለሳ ጀምሮ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የመረጃ ተዓማኒነት እንዲኖር ለማስቻልም የትራፊክ አደጋ ምዝገባን በሲስተም ለመመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም