ቀጥታ፡

የ"ኩል ፖርት አዲስ'' ፕሮጀክት ግንባታ ዘንድሮ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ የሚውለው የ"ኩል ፖርት አዲስ'' ፕሮጀክት ግንባታ ዘንድሮ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ የወደብና ተርሚናል ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ምህረተአብ ተክሉ፤ ኢትዮጵያ በፍራፍሬና አትክልት ዘርፍ ያላትን ዕምቅ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል አስፈላጊው መሰረተ ልማት ማሟላት እንደሚገባ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ የምርቶችን ጥራት ጠብቆ ወደ ውጪ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የማቀዝቀዣ  ኮንቴነሮችን መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል። 

ከዚህ አኳያ በሞጆ ደረቅ ወደብ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቆያና መጓጓዣ የሚውል "ኩል ፖርት አዲስ" ፕሮጀክት መሰረት ድንጋይ ከስድስት ዓመት በፊት መቀመጡን  አስታውሰዋል፡፡ 

ይሁንና ግንባታውን ለመጀመር የሚውል ፋይናንስ በሚፈለገው ጊዜ አለማግኘትና በዘርፉ በቂ ልምድ ለማግኘት የሚያስችሉ ጥናቶች መጓተት ፕሮጀክቱ በተባለለት ጊዜ እንዳይጀመር ማድረጉን አብራርተዋል።

ለፕሮጀክቱ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ከኔዘርላንድስ መንግስት ጋር የረዥም ጊዜ ውይይትና ድርድር ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸው፤ ይህን ተከትሎም ከወራት በፊት የ25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ በ50 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን ቀሪው 25 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈንም ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም የፕሮጀክቱ ግንባታ በዘንድሮው ዓመት እንደሚጀመርና በሁለት ዓመት ወስጥ እንደሚጠናቀቅ አረጋግጠዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ውጪ እንዲላኩና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኙ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሞጆ ደረቅ ወደብ የነዳጅ አቅርቦቱን አስተማማኝ በማድረግ የካርጎ አገልግሎትን ማሳለጥ የሚያስችል የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣዩ ወር ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ፕሮጀክት የነዳጅ አቅርቦቱን አስተማማኝ በማድረግ ቀልጣፋ የካርጎ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም