የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ ለመተካት ወደተግባር ተገብቷል

ዲላ ፤ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ ለመተካት ወደተግባር መገባቱ ተገለጸ።

በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ ተሞክሮን ለመለዋወጥ ያለመ የመስክ ምልከታ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል።

በመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉት የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ የአማራና የጋምቤላ ክልሎች የዘርፉ አመራሮች እንደገለጹት፣ በየክልላቸው የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው። 

በዚህም በተያዘው የሚያዚያ ወር ከ96 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ተከላ ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን የቡና ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አማኑኤል ብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በ221 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡና ይለማል። 

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘንድሮ ያረጁ የቡና ተክሎችን በመተካትና አዲስ የቡና ማሳ በማስፋት ከ8ሺህ 800 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ቡና ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለተከላ ከተዘጋጁ 35 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ውስጥ 32 ሚሊዮኑ በተያዘው ሚያዚያ ወር ተከላቸው እንደሚከናወን ተናግረዋል። 


 

ክልሉ ለቡና ልማት ያለውን ያልተነካ አቅም በሚገባ ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሆርቲካልቸርና መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ተሻለ አይናለም ናቸው።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ ከዓመታዊ ሰብሎች በተጓዳኝ የቡናና ቅመማ ቅመም ምርቶች ያላቸውን ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው። 

ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ከ7 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል በክልሉ በቡና የተሸፈነ መሬት ከ28ሺህ 300 ሄክታር በላይ ለማድረስ ተችሏል።

ዘንድሮም በ12 የችግኝ ጣቢያዎች ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ በተያዘው ሚያዚያ ወር 7 ሚሊዮን 700 ሺህ ችግኝ ይተከላል ብለዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስራት መኩሪያ በበኩላቸው እንደገለጹት በክልሉ 560ሺህ ሄክታር ላይ ቡና በተለያዩ መንገዶች እየለማ ይገኛል። 

በእዚህም ክልሉ በቡና ምርት አቅርቦትና በወጪ ንግድ ቀዳሚ መሆኑን አንስተው፣ በተያዘው ዓመት ከ59 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የዘር ቡና በክልሉ በማዘጋጀት ከራሱ ባለፈ ለአጎራባች ክልሎች ጭምር የዘር ምንጭ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።

በቡና እደሳት በተለይ ያረጀ የቡና ተክልን ነቅሎ በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች የመተካቱ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል ያሉት አቶ አስራት፣ በተያዘው ዓመት ከ3ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ የቡና እድሳት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በታደሰና በአዲስ መሬት በክልሉ ከ70 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ዘንድሮ እንደሚተከሉና 42 ሚሊዮኑ በተያዘው ወር ተከላቸው የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል።


 

በጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ምርት ጥራት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ዘውዴ በበኩላቸው በክልሉ ሦስት ወረዳዎች በ61 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡና  በአርሶ አደሮችና በአልሚ ባለሀብቶች እንደሚመረት ተናግረዋል።

ይሁንና በአንዱ ወረዳ ከሚገኘው የቡና ተክል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው በእርጅና ምክንያት ከምርት ውጭ በመሆኑ የእድሳት ሥራው በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

"በተያዘው ዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለመትከል እየተሰራ ነው" ያሉት አቶ እሸቱ፣ ይህም በክልሉ በሄክታር የሚገኘውን 6 ነጥብ 6 ኩንታል አማካኝ ምርት ወደ 9 ኩንታል ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረወዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ ቡና ከሚለማባቸው የአገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ ሥራ ሃላፊዎችና አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የመስክ ምልከታ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም