አካባቢን መንከባከብና የተፈጥሮ ውበትን  ማቆየት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት ነው

ሠመራ፤  ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ አካባቢን መንከባከብና የተፈጥሮን ውበት ማቆየት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዓሊ መሐመድ ተናገሩ።

"ብክለት ይብቃ-ውበት  ይንቃ" በሚል መሪ ሐሳብ  የተጀመረው አገር  አቀፍ የአካባቢ ብክለትን የማስወገድ ንቅናቄ በአፋር ክልል ደረጃ የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ዛሬ በሠመራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዓሊ መሐመድ እንዳሉት አካባቢን መጠበቅ በተለይም የሰው ልጆችን አኗኗር በበጎ ሁኔታ መያዝና ደህንነቱን መጠበቅ ነው።

ዜጎች በንፁህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብታቸው እንዲከበር የክልሉ መንግስት በርካታ ጥረቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ ዓሊ አስረድተዋል።

የአካባቢ ብክለት በዓለማችን በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ዓሊ፤ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የተቀናጀ ተሳትፎ የሚያሻው መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢን ፅዳትና ውበት ችላ ማለት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማዛባቱም ባሻገር የከተሞቻችንን ብሎም የሐገራችንን ገፅታ በእጅጉ ያጎድፋል ብለዋል።

በመሆኑም በሁሉም የልማት ዘርፎች ላይ የጀመርናቸው የነቃ ተሳትፎን በማጠናከር አካባቢያችንን አረንጓዴ ውብና ሳቢ ማድረግ ያሻል ብለዋል።

የክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ ገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው በክልሉ ያሉት አደረጃጀቶች እየሰፉና ከተሞች እያደጉ መምጣታቸው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በተለይም የፕላስቲክ ብክለትን ለማስወገድ በቀዳሚነት የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ እንዳሉት የኘላስቲክ፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈርና የድምፅ ብክለቶቾ በአካባቢ ብክለት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

ይህ የንቅናቄ መርሐ ግብር ብክለትን የሚያስከትሉ መንስዔዎች ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢ ብክለት በከፍተኛ ደረጃ የጤና ጠንቅ እያስከተለ በመሆኑ በተለይሞ የኘላስቲክ ብክለት ለመቀነስ ንቅናቄው አስፈላጊ መሆኑን  አስገንዝበዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም