በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ለበልግ አብቃይ አካባቢዎች አመቺ ነው

145

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የዝናብ  ሁኔታ ቀደም ብለው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎች እንዲሁም ቋሚ ተክሎች አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በቀጣዩቹ አስር ቀናት በደቡብ፣ በምስራቅ፣ በሰሜን ምስራቅና በመካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አመልክቷል።

በመሆኑም የሚጠበቀው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት ለሟሟላት እንዲሁም የመኸር ሰብሎችን ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ ለመዝራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

አርሷአደሩ የሚገኘውን እርጥበት ለመጠቀም የሚያስችል አስፈላጊውን የግብዓት ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ተመላክቷል።

የሚጠበቀው እርጥበት ለእንስሳት መኖና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው በመደበኛ ሁኔታ ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎችን በማሳም ሆነ ከማሳ ውጪ የውሃ እቀባ ስራዎችን በተገቢው ማከናወን ይገባቸዋል ።

በሌላ በኩል በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚጠበቅም የሚቲዎሮሎጂ ትንበያው ያመላክታል።

ይህ ሁኔታ በተወሰኑ ውሃ ገብ በሆኑና በወንዝ ዳርቻ ባሉ ማሳዎች ላይ የውሃ መተኛትና የአፈር መታጠብን ሊያስከትል ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም መግለጫው አሳስቧል።

ከቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ጎን ለጎን የሚገኘውን እርጥበት በላቀ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም ተገልጿል።

በተጨማሪም በቀጣዮቹ አስር ቀናት በአፋር ደናክል፣አዋሽ ስምጥ ሸለቆ፣ገናሌዳዋ እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት የሚኖር ሲሆን በሌሎች ተፋሰሶች ላይ ደግሞ ከመጠነኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ይኖራቸዋል።

ይህ ሁኔታ በየተፋሰሶች የሚገኙት የውሃ አካላት የተሻለ የውሃ መጠን እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።

ለመስኖም ሆነ ለሃይል ማመንጨት የሚያገለግሉ የግድቦችን የውሃ መጠን የሚያሻሻል በመሆኑ ይህንኑ እድል ለመጠቀም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ተብሏል።   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም