የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባለፉት 9 ወራት የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎቶች ሰጠ

207

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባለፉት 9 ወራት የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።

ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በዋናነት የጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪ፣ የጥራት ሰርተፊኬሽን እና የኢንስፔክሽን አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

በዚህም ባለፉት 9 ወራት ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ከ19 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ምርቶች በላብራቶሪ የጥራት ፍተሻና የሰርተፊኬሽን አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

ጅቡቲ በሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍም  ከ31 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ላይ የላቦራቶሪ ፍተሻ ማድረጉን ነው ያነሱት።

ድርጅቱ የጥራት ፍተሻ አገልግሎት ከሚሰጣቸው ዘርፎች መካከል የግብርና ግብዓቶች፣ የምግብና መጠጥ፣ መድሃኒት፣ ኬሚካልና ማዕድን፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ የኤሌክትሮኒክስ የቆዳና ጨርቃጨርቅ ምርቶች ይገኙበታል።

ምርቶቹ በተቀመጠላቸው መስፈርት መሰረት ደረጃቸውን ጠብቀው መመረታቸው ተፈትሾ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተሰጣቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ድርጅቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተቀባይነት ያላቸው መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

የፍተሻ ላቦራቶሪዎቹ ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው በመሆናቸው የህብረተሰቡን ደህንነትና ጤንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።

በመንግስት ከውጭ የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች የተቀመጠላቸውን የጥራት መስፈርት ማሟላታቸውን ማረጋገጥ ላይ ልዩ ትኩረት መደረጉንም  ተናግረዋል።

ድርጅቱ የጥራት ፍተሻና የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከሰጠ በኋላም በምርቶቹ ላይ በየሶስት ወሩ ፍተሻ እንደሚያደርግ ነው ያነሱት።

ፍተሻ ተደርጎባቸው ከሁለት ጊዜ በላይ የተቀመጠላቸውን የጥራት መስፈርት ያላሟሉ ምርቶችን ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል በማሳወቅ በምርቶቹ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በየክልሉ 9 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ህብረተሰቡ አስገዳጅ የጥራት ምልክቶችና የምርት ደረጃዎች ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ከባለደርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም