በክልሉ የአካባቢ ብክለትን በማስወገድ ምቹ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ 

174

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት በማስወገድ ለሰዎች ተስማሚ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ህብረተሰብ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ።

"ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሀሳብ ብክለትን መከላከልና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ እንደገለጹት፤ አካባቢን ከብክለት በመጠበቅ ለሰው ልጅ ተስማሚ የሆነ ስነ ምህዳር ለመፍጠር በተቀናጀ መንገድ መስራት ይገባል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያዚያ ወር 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለአካባቢ ጥበቃ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በየአካባቢው በዘፈቀደ የሚጣሉ ፕላስቲኮችን ዘወትር በማፅዳት አካባቢን ከብክለት ነፃ የማድረግና ስነ-ምህዳርን በዘላቂነት የመጠበቅ ሥራ የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያም ብክለት እያስከተለ ያለውን አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል ለህብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

በከተሞች የሚስተዋለውን የፕላስትክ ቆሻሻ የማስወገድ ብቻ ሳይሆን መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ እንዲፈጠር በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አረጋ አመልክተዋል 

''ብክለት የአካባቢን ስነ-ምህዳር ከመጉዳት ባለፈ ህይወት ላላቸው አካላት የሞት መንስኤ ነው'' ያሉት ደግም የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ናቸው።

ከብክለት ነፃና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር በተለይ ከተሞችን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ለማድረግ ባለስልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የአካባቢ ብክለትን መከላከል ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የእቅዳቸው አካል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም