​​​​​​​በናይል ተፋስስ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብር ወሳኝ ነው- የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦ በናይል ተፋስስ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ዘላቂነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ገለጸ። 

የናይል ተፋስስ ኢኒሼቲቭ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 ሀገራትን ያቀፈው ኢኒሼቲቩ የተፋሰሱን ፀጋዎች በጋራ በማልማት ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ዓላማ አለው።

25 ዓመታትን ያስቆጠረው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በትብብር ማልማት፣ የውሃ ሀብት ስራ አመራር እና የውሃ ሀብቶች ልማት ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣናው ፈተናዎችን በመሻገር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሐዊ አጠቃቀም እና የውሃ ሀብት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ሀገራት ትብብርና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህም የሀገራቱን የጋራ ህልም፣ አንድነትና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞችን ገቢራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ኢኒሼቲቩ በአቅም ግንባታ እና ምክክር ላይ እየሰራ ሲሆን የተፋሰሱን ህዝብ ኑሮ የሚያሻሽሉ ዉሃ ነክ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እየሰራ ነው ብለዋል።

በሰላምና ደህንነት፣ በውሃ ዋስትና፣ በኃይል፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በምግብ ዋስትና ያሉ ፈተናዎችን ለመሻገር እንደ ሀገርና እንደ ተፋሰስ በትብብር መስራት ይገባል ነው ያሉት። 

ከሌሎች ቀጣናዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ፣ ስራ ፈጠራና ድህነት ቅነሳ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭን ወደ ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ቀጣናዊ ተቋም ለማሸጋገር የተደረሰውን የሕግ ማዕቀፍ ያልፈረሙ አባል ሀገራት እንዲፈርሙም ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ በበኩላቸው፤ ኢኒሼቲቩ በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።

የጋራ ፕሮጀክቶች እንዲተገበሩ በማድረግ ለሀገራዊና ቀጣናዊ ስራዎች ጉል አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የሀገራቱን የጋራ ግብ ዕውን ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እየተሳሰረች መሆኑን ገልፀው፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ግድቦች ከራሷ አልፎ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጎርፍና ሌሎች አደጋዎችን በመቀነስ ረገድ ያላቸውን ወሳኝ አስተዋፅኦ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነት ዕውን እንዲሆን አበክራ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

የሀገራቱ የጋራ አደረጃጅት የሆነው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ወደ ሕጋዊ ቀጣናዊ ኮሚሽን እንዲሸጋገር ያላትን ፅኑ መሻት ገልፀው፣ ሀገራቱም ስምምነቱን ማፅደቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም