በብሄራዊ ፓርኩ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ   እንዳይዛመት መከላከል ተቻለ

101

ጎንደር ፤ሚያዚያ 14 /2016(ኢዜአ)፡- በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ  እሳቱ እንዳይዛመት መከላከል መቻሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የአግሮ ኢኮሎጂና የዱር እንስሳት ተመራማሪ አቶ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የእሳት ቃጠሎው የተነሳው በፓርኩ ክልል አምባራስ በተባለው ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡

የእሳት ቃጠሎው የተነሳው ሚያዚያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም  ጠቅሰው፤ ቃጠሎው በተነሳበት አካባቢ በጓሳ ሳርና ውጨና በተባሉ የፓርኩ የተፈጥሮ የደን ዛፎች ላይ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል፡፡

በፓርኩ የዱር እንስሳት ላይ እስካሁን ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ጠቁመው፤ የቃጠሎው ምክንያት በውል አለመታወቁንም ተናግረዋል።

በፓርኩ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ አባላት፣ በነዋሪዎችና በአጋር አካላት ተሳትፎ በተደረገው የመከላከል ስራ ግጭና እሜት ጎጎ በተባሉ ጎጦች ቃጠሎውን በመቆጣጠር ወደ ፓርኩ የተለያዩ አካባቢዎች እንዳይዛመት መከላከል መቻሉን አስታውቀዋል፡፡


 

ሙሉ በመሉ ለመቆጣጠርም ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። 

የአካባቢው ሞቃታማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ለቃጠሎው መባባስ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፤ እሳቱ ያደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር ለማወቅ በቀጣይ ቀናት በሚቋቋም ግብረ ሃይል ጥናት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በፓርኩ ክልል ባለፉት ዓመታት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በቃጠሎው ጉዳት የደረሰበትን የፓርኩን የተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ በኩልም በየዓመቱ ክረምት ሀገር በቀል ችግኞች በመትከል የክብካቤ ስራ ሲከናወን መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡

412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ፓርኩ ውስጥ  ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም