በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ስርዓትን ማጠናከር ይገባል--በለጠ ሞላ( ዶ/ር)

125

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 14/2016 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ ( ዶ/ር) ገለጸ።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ግብርናን በማስፋት በምግብ ራስን ለመቻል በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለሁለት ቀናት እየተካሄደ በሚገኘው ስድስተኛው የአፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ነው።

ጉባኤው “የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳን ለማሳካት እና በ2063 በአፍሪካ ድህነትን ለማጥፋት የቴክኖሎጂና የፈጠራ መፍትሔዎችን በአግባቡ መተግበር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢኖቬሽንና ቴከኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) አፍሪካ ተስፋ ሰጪ ጉዞ ላይ ብትሆንም ያልተሻገረቻቸው ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ድህነት፣ የሰላምና ፀጥታ ችግርና የልማት አለመረጋገጥ ከፈተናዎች መካከል ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ አፍሪካን ካለችበት ችግር ለማውጣት ወሳኝ መሳሪያዎች ናቸው ብለዋል።

በግብርና፣ በታዳሽ ሃይል እና በጤናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በመተግበር የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል፣ ስራ ፈጠራን ማስፋት እና ድህነትን መቀነስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ስራዎችን ለመተግበርም ተቋማት በባህል ለውጥና በፖሊሲ አተገባበር ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የመንግስት ተቋማት፣ የግል ዘርፍ፣ የምርምር ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የእውቀት፣ የሀብትና የሙያ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

ለዚህም የስርዓተ ምግብ ሽግግር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ምርታማነትን ለማሳደግና ከተረጂነት ለመላቀቅ ቴክኖሎጂ መር ልማት እየተተገበረ ነው ብለዋል።

 ከዚህም ባሻገር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመቅረፅ በሀገሪቱ  መሰረታዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትግበራ እየተከናወነ መሆኑንም አውስተዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው፥ አፍሪካ  እንድታድግ የሰው ሀይል ልማት፣ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ በትኩረት መስራት አለባት ብለዋል።

አህጉሪቱ በሰብል ምርት፣ በእንስሳትና በአሳ ሀብት ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፥ ይህን ወደ ጥቅም ለመቀየርና የሚሊዮኖችን ህይወት ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ግብርና ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም