የሜካናይዝድ ሃይል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጸንቶ እንዲቆይ የተጫወተውን የላቀ ሚና ለማስቀጠል ዘመኑን በሚዋጅ ብቃት የማጠናከር ስራ ይከናወናል − ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን

179

አዋሽ አርባ፤ ሚያዝያ 13/2016(ኢዜአ)፡- የሜካናይዝድ ሃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተጠብቆና  ፀንቶ እንዲቆይ የተጫወተውን የላቀ ሚና ለማስቀጠል ዘመኑን በሚዋጅ ብቃትና ጥራት የማነጽ ተግባር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሜካናይዝድ ዕዝ የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት 46ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች በተገኙበት ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በዚህ ወቅት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ዋና አዛዥና የዕለቱ የክብር እንግዳ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ ያፈራቸው የሜካናይዝድና ሞተረኛ የሰው ሃይል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን በማፅናት ረገድ ወሳኝ የላቀ ሚና ተጫውቷል።


 

ይህን የላቀ ሚናውን ለማስቀጠል የሜካናይዝድ የስልጠናና ስርዓተ ትምህርት በመከለስና በአዲስ መልክ በማዘጋጀት ዘመኑን የዋጀ የውጊያ ቴክኒክ ስልጠናና የዘርፉ የሰው ሃይል ልማት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይም የመከላከያ ፍላጎትን ያገናዘበ በሜካናይዝድ ቴክኖሎጂ ዕውቀት፣ ክህሎትና አጠቃቀም የበቁ ምድብተኞች፣ አመራሮችና አሽከርካሪዎች ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

በተለይ ትምህርት ቤቱ የሜካናይዝድ የትምህርትና ስልጠና የልህቀት ተቋም ለማድረግ በዘርፉ የተጀመሩ ሪፎርም ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ትምህርት ቤቱን በዘመናዊ የሜካናይዝድና ሞተራይዝድ ቴክኖሎጂ በማደራጀት ስልጠና እንዲሰጥ መደረጉን ገልጿል።


 

ዘመናዊ ትጥቆችን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል በስልጠናና በዲስፕሊን የታነፀ ዘመኑን የሚዋጅ ብቃት ያላቸውን ሜካናይዝድ ሙያተኞችን በጥራትና በብዛት ለማፍራት እየሰራን ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት 46ኛውን የምስረታ በዓል ትምህርት ቤትን አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለመውሰድ የመከላከያ ተቋምን ዕቅድና ፍላጎት በዘላቂነት ለማሳካት ቃል የሚገባበት መሆኑን አስረድተዋል።


 

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሜካናይዝድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ በበኩላቸው፤  ትምህርት ቤቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሁሉም የሜካናይዝድ ቴክኖሎጂ የበቁና የግዳጅ ተልዕኮውን በከፍተኛ ደረጃ መፈጸም  የሚችል ሃይል የመገንባት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በተለይ ከወቅቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር መራመድ የሚችል የሜካናይዝድና ሞተራይዝ ሃይል ግንባታና የዘመኑ የስልጠና ቴክኖሎጂን አጠቃቀም ላይ የመከላከያ ሃይሉን አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።


 

ትምህርት ቤቱ በ1970 ዓ.ም ሲመሰረት በወቅቱ በምስራቁ ክፍል የነበረውን ወረራ ለመመልከት ነበር ያሉት ደግሞ የአዋሽ አርባ የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ባለው ምንተስኖት ናቸው። 

ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የታንከኛ፣ መድፈኛና ሞተራይዝድ ክፍሎች በማብቃት በየዘመኑ የተቃጡ ወረራዎችን በማክሸፍ ሚናውን መወጣቱን ተናግረዋል።

ሰፊ ክህሎትና ልምድ ያለበት ከመሆኑም ባለፈ የስነ ልቦናና አዲስ የስልጠና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የተሻለ  የመካናይዝድ አቅም ለመፍጠር አሁንም በሙሉ አቅማችን እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የባለፉት 46 ዓመታት የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት የዕድገት ጉዞና አሁን ያለበት ደረጃን የሚያሳይ የፎቶና መካናይዝድ አውደ ርዕይ በእንግዶች ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም