በጋምቤላ የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው

88

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 13/2016(ኢዜአ)-  በጋምቤላ ክልል መጪውን የክረምት መግቢያ ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስፈላጊው የቅድመ መከላከል ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የወባ መከላከል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አዲሱ ጦና ለኢዜአ እንደገለጹት ሁሉም የክልሉ ወረዳዎች የወባ ተጋላጭ በመሆናቸው የቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ ስራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ ናቸው።

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የክረምቱን መግቢያና መውጫ ተከትሎ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በተለየ በሽታው ጨምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም ባለፉት ሁለት ዓመታት በክረምቱ መግቢያና መውጫ የነበረው ዓይነት የወባ በሽታ ዳግም እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ማሰራጨት፣ የፀረ- ወባ ኬሚካል ርጭት ማካሄድ፣ የአካባቢ ጽዳትና ቁጥጥር ስራዎች ማጠናከርና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል እየተሰሩ ከሚገኙ የመከላከል ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በበሽታው የተያዙ ሰዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አስፈላጊው የህክምና ግብዓት ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በአራት ከፍተኛ የወባ ተጋላጭ ወረዳዎች የአጎበር ስርጭት እንደሚካሄድ ጠቁመው በዲማና በጎደሬ ወረዳ ከሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ 50 ሺህ አጎበሮች ለማሰራጨት ታቅዷል ብለዋል።

እንዲሁም በክልሉ አስር ወረዳዎችና ስድስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከ148 ሺህ በሚበልጡ ቤቶች ላይ የፀረ- ወባ ኬሚካል ርጭት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጀት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።

ከተጠቀሱት ስራዎች ጎን ለጎንም በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም፣ አካባቢን በማጽዳት ወባን መከላከል እንደሚቻል ማህበረሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሮን ጉኝ እንዳሉት በበጋው ወራትም በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢኖሩም በክረምቱ መግቢያና መውጫ ወቅት በበሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል ብለዋል።

ሆስፒታሉ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የክረምቱን መግቢያ ተከትሎ ለሚጨምረው የወባ በሽታ አስፈላጊው የህክምና ግብዓት መቅረቡን ጠቁመው ወደ ህክምና ለሚመጡት ታካሚዎች ስለ በሽታው ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የወባ በሽታ በበጋ ወራት የሚቀንስ ቢሆንም በክረምት ወራት በጅጉ እንደሚጨምር የገለጹት ደግሞ በሆስፒታሉ ሲታከሙ ያገኘናቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ጋድቤል ቤል ናቸው።

በመሆኑም በክረምቱ ወራት አካባቢያቸውን በማጽዳትና የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም ከበሽታው እራሳቸውን ለመጠበቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ነው ታካሚው የገለጹት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም