የአምራች ኢንዱስትሪውን የምርትና የተወዳዳሪነት አቅም የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪውን የምርትና የተወዳዳሪነት አቅም የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡- አምራች ኢንዱስትሪዎችን በፋይናንስና ግብዓት በመደገፍ የምርትና የተወዳዳሪነት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
በ2014 ዓ.ም የተጀመረው "ኢትዮጵያ ታምርት" እንቅስቃሴ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ታግዞ ንቅናቄው አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ዘንድሮ የተዘጋጀው የ"ኢትዮጵያ ታምርት" የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመርሃ-ግብሩ ላይ በመታደም ውድድሩን ያስጀመሩ ሲሆን፤ ታዋቂ አትሌቶች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ሠራተኞችና ኢንዱስትሪን የሚደግፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደገለፁት፤ አምራች ኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲያስተዋውቁና ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህላቸውን እንዲሳድጉ ግንዛቤ ለመፍጠር ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪውን ማኅበረሰብ ከስፖርት ጋር በማስተሳሰር፣ የገበያ ትስስርን ለመፍጠርና ጤናማ የሆነ አምራች ዜጋ ለማፍራት መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በመሠረተ- ልማትና ሌሎችም ቅንጅታዊ ጥረቶች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም አስታውሰዋል።
የአሠራር ሥርዓትና የሕግ ክፍተቶችን በማረም ለመሥራት የሚያስችሉ አዳዲስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ያስቻለ መሆኑንም አቶ መላኩ ተናግረዋል።
በቀጣይም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በፋይናንስና በግብዓት በመደገፍ የምርትና የተወዳዳሪነት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሩጫ ውድድር አትሌቶች ዓላማውን ከመደገፍ ባለፈ በርካታ ወጣት አትሌቶች አቅማቸውን የሚያሳዩበት መሆኑን ተናግሯል።
የሩጫ ውድድሩ አምራችነትን ከማበረታታት ባለፈ የአንድነት፣ የአብሮነትና የሰላም መገለጫ መሆኑንም ጠቅሷል።
በውድድሩ በወንዶች አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው አትሌት ገመቹ ዲዳ፤ ለአዳዲስ አትሌቶች መነሳሳትን የሚፈጥርና ታዋቂ አትሌቶችን ደግሞ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግሯል።
ከ10 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት ሩጫ በርካታውን ቁጥር የያዙት የኢንዱስትሪ ሠራተኞችና ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ከ27 ክለቦች የተውጣጡ 538 አትሌቶችም ተሳትፈዋል።
በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች አንደኛ ሆነው ላጠናቀቁ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 250 ሺህ ብር እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
በውድድሩ ሁለተኛና ሦስተኛ ለወጡትም በቅደም ተከተላቸው 150 ሺህ እና 100 ሺህ ብር ተሸልመዋል።