ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ተኪ ምርቶች ተመርተዋል

ደሴ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡- በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ተኪ ምርቶች ማምረት መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በተጨማሪም ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ90 ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገቢ መገኘቱንም ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተኪ ምርት በማምረት፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንዲሁም ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተደረገ ጥረት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው ተኪ ምርቶች ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይ መድሃኒትን ጨምሮ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ወጪ ያስወጡ የነበሩ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸው የተጀመረውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሳካት እያገዙ ናቸው ብለዋል።

ህብረተሰቡም የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀምና በሀገር ምርት የመኩራት ልምዱን ሊያጠናክር እንደሚገባም አመልክተዋል።

እንዲሁም በ13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች በዓለም ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ምርት እያመረቱ በማቅረብም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን እያገዘ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ ምርታማነትን ለመጨመር፣ ተኪ ምርትን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም