ቀጥታ፡

የሜካናይዝድ ሃይል የኢትዮጵያ  ሉዓላዊነት ፀንቶ እንዲቆይ የተጫወተው  ሚና የላቀ ነው- ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን 

አዋሽ አርባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡-  የሜካናይዝድ ሃይል  የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆና   ፀንቶ እንዲቆይ   የተጫወተው ሚና የላቀ መሆኑን የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ተናገሩ።

የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት 46ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከፍተኛ የመከላከያ ጄኔራል መኮንኖች በተገኙበት ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በዚህ ወቅት ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እንደገለጹት፤ትምህርት ቤቱ ያፈራቸው የሜካናይዝድና ሞተረኛ የሰው ሃይል  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማፅናት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

የዚያድ ባሬ ወራሪ በወቅቱ ቃጥቶት የነበረውን  ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት የላቀ  አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም በአነስተኛ የሰብዓዊ ሃይል ኪሳራ ድል እየተቀዳጀ የመጣ መሆኑን አውስተው፤ አሁንም የሜካናይዝድ ክፍሎች የጎላ ሚናቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዘመናዊ ትጥቆችን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል በስልጠናና በዲስፕልን የታነፀ ዘመኑን የሚዋጅ ብቃት ያላቸውን ሜካናይዝድ ሙያተኞችን በጥራትና በብዛት ለማፍራት እየሰራን ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሜካናይዝድ ዕዝ የአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት 46ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ስናከብር ትምህርት ቤቱን አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለመውሰድ የመከላከያ ተቋምን ዕቅድና ፍላጎት በዘላቂነት ለማሳካት ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል።

በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሜካናይዝድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ በበኩላቸው፤  ትምህርት ቤቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ አገሪቱ በሁሉም የሜካናይዝድ ቴክኖሎጂ የበቁና የግዳጅ ተልዕኮውን በከፍተኛ ደረጃ መፈጸም  የሚችል ሃይል የመገንባት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ።

በተለይ ከወቅቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር መሄድ የሚችል የሜካናይዝድና ሞተራይዝ ሃይል ግንባታና የዘመኑ የስልጠና ቴክኖሎጂን አጠቃቀም ላይ የመከላከያ ሃይሉን አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል ።

ትምህርት ቤቱ በ1970 ዓ.ም ሲመሰረት በወቅቱ በምስራቁ ክፍል የነበረውን ወረራ ለመመከት ነበር ያሉት ደግሞ የአዋሽ አርባ የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ባለው ምንተስኖት ናቸው። 

ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የታንከኛ፣ መድፈኛና ሞተራይዝድ ክፍሎች በማብቃት በየዘመኑ የተቃጡ ወረራዎችን በማክሸፉ  ሚናውን መወጣቱን ተናግረዋል።

ሰፊ ክህሎትና ልምድ ያለበት ከመሆኑም ባለፈ የስነ ልቦናና አዲስ የስልጠና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የተሻለ  የመካናይዝድ አቅም ለመከላከያ ለመፍጠር አሁንም በሙሉ አቅማችን እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የባለፉት 46 ዓመታት የውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት የዕድገት ጉዞና አሁን ያለበት ደረጃን የሚያሳይ የፎቶና መካናይዝድ አውደርዕይ በእንግዶች ተጎብኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም