የፕሪሚየር ሊጉ 22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል

240

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።

በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ኢትዮጵያ ቡና ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት ሲጫወቱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ደግሞ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ፣ በሶስቱ ሽንፈት ገጥሞች አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በዚሀም መሰረት በሊጉ በ33 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

መቻል በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲያደርግ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በዚህም መሰረት መቻል በ40 ነጥብ በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ 22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ይጨወታሉ።

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከሲዳማ ቡና ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በ43 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ፣ አንድ ጊዜ ተሸንፎ፣ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላጋጠመውም።

በሁለቱ ሲያሸንፍ በሶስቱ አቻ ወጥቶ በ27 ነጥብ በሊጉ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሊጉ 22ኛ ሳምንት ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ሻሸመኔ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

የዛሬ ጨዋታዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የድሬዳዋ ቆይታ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከ16ኛ ሳምንት አንስቶ የሊጉ ጨዋታዎች በድሬዳዋ ስታዲየም ሲደረጉ እንደነበር ይታወቃል።

ከ23 እስከ 27ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚደረጉ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም