የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሕግ ማዕቀፍ እርምጃዎች የዲፕሎማሲ በር ከፍተዋል - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሕግ ማዕቀፍ እርምጃዎች የዲፕሎማሲ በር ከፍተዋል - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሕግ ማዕቀፍ እርምጃዎች የዲፕሎማሲ በር መክፈታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
በተለይም በቅርቡ ለውጭ ኩባንያዎች የተፈቀዱ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ጋር ያላትን መስተጋብር የሚያጎለብቱ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እድገት የሚበጁ ናቸው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቁልፍ አጀንዳዎች መካከል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከአፍሪካና ከዓለም ጋር ማስተሳሰር አንዱ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር የተወሰዱ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻላቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት አባል መሆኗን እንዲሁም በዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን የሚያስችል ድርድር እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ ለቀጣናው ሀገራትም ሆነ ለዓለም ዕድል እንጂ ስጋት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ውስጣዊ ኢኮኖሚያዊ አቅም መጎልበት የትብብር ማዕከል በመሆን ለዲፕሎማሲው ዘርፍ መጠናከር ጉልህ ሚና ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ነጻ ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረቱ ኢኮኖሚውን ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያስተሳስራል ብለዋል።
ለአብነትም የውጭ ኩባንያዎች ቀደም ሲል ባልተፈቀዱ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ የወጣው መመሪያ ኢትዮጵያን ከሀገራት ጋር ለማስተሳሰር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፍላጎትና መተማመን እንዲጨምር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማቃለል እና ለሸቀጦች ዋጋ መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ሀገራት በትብብር እንጂ በተናጠል ቆመው ብልጽግናቸውን ማረጋገጥ እንደማይችሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ውስጣዊ ሰላም፣ ልማትና ደህንነትን መሰረት ያደረጉ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የትብብር ስምምነቶች ማድረጓን አውስተዋል።
የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ የትብብር ስምምነቶችን መፈረም ብቻ ሳይሆን ገቢራዊ ተደርገው ውጤት እያስገኙ መሆኑንም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነቶችን መሰነድ እና በየወቅቱ በመከለስ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት የሚያስጠብቁ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ አበክሮ እየሰራ ነው ብለዋል።