በሀረሪ ክልል በዘንድሮው አመት 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡- በሀረሪ ክልል በዘንድሮው አመት 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ገለፁ፡፡

ወይዘሮ ሮዛ ኡመር የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አስመልክተው እንደገለፁት ከሚተከሉ ችግኞች መካከል ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የተለያዩ አይነት ፍራፍሬዎች ናቸው፡፡

ይህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረትና የአፈርና ውሃ ጥበቃን የሚያሻሽሉ ሌሎች የደን ዛፎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተመናመኑ የሚገኙ የፍራፍሬ ዝርያዎች እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የጎርፍ ተጋላጭነትን በሚቀንስና የችግኝ ፅድቀት መጠንን በሚያሳድግ መልኩ የተፋሰስ ልማት ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የችግኝ ጣቢያዎችም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሚተከሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞች ውስጥ 70 በመቶው የጥምር ደን ሲሆን 30 በመቶው ደግሞ የደን ዛፍ መሆኑን ገልጸዋል።

እየተደረጉ የሚገኙ ዝግጅቶችን በሚመለከት የችግኝ ጣቢያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ከወትሮው በተለየ መልኩ የተለያዩ ችግኞችን የማዳቀል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የተያዘው እቅድ እንዲሳካ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም