አለም አቀፉ የታዳሽ ሀይል ኤጀንሲ ኢትዮጵያ የቀጣናው ሀገራትን በታዳሽ ሀይል ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት አደነቀ

183

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡-  አለም አቀፉ የታዳሽ ሀይል ኤጀንሲ ኢትዮጵያ የቀጣናው ሀገራትን በታዳሽ ሀይል ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት አድንቋል።

አራተኛ አለም አቀፍ የታዳሽ ሀይል ኤጀንሲ ጉባኤ በአቡ ዳቢ ከተማ  ተካሄዷል።

በጉባኤው ላይ  የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)  እና  በኢትዮጵያ በአረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡማር ሁሴን ተሳትፈዋል።


 

በጉባኤው አራተኛ ቀናት ታዳሽ ሀይል ማከማቸት በሚቻልበትና በአፍሪካ የሀይል አቅርቦት ሽግግርን፣ ታዳሽ ሀይልን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮዎችና የዘርፉን  የፖሊሲ ማእቀፎች ላይ ምክክር ተደርጓል።

እአአ በ2030 አባል ሀገራት ታዳሽ ሀይልን ጥቅም ላይ ለማዋል በጋራ የሚሰሩበትን አቅም  ማጉላት የሚቻልበትን ሁኔታን ማጠናከርም  የውይይቱ አካል እንደነበር ተገልጿል።

በምክክሩ ላይ የውሀና  ኢነርጂ ሚኒስትሩ  ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ታዳሽ ሀይልን ለማበረታታት የመንግስትና የግል አጋርነት ፖሊሲን በመተግበር በጸሀይ ሀይል፣ በንፋስና በእንፋሎት ሀይል የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን መተግበሯን  አንስተዋል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተቀየሰው የታዳሽ  የሀይል ስትራቴጂም በአፍሪካ በ2030 የሀይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የተጣለውን  ግብ ሙሉ በሙሉ  ለማሳካት መቃረቧን ጠቁመዋል።

በዚህም መንግስት  የቀጣናውን ሀገራት በሀይል አቅርቦት ለማስተሳሰር  ለኬንያ ፣ለጅቡቲና ለሌሎች ሀገራት ሀይል ማቅረቡን ሲያስታውሱ ይህም ከሀይል አቅርቦት ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት መስፈን ትልቅ አቅም  ማበርከቱን  ተናግረዋል።


 

የአለም አቀፉ የታዳሽ ሀይሎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አልፋሮ ፔሊኮ  በበኩላቸው  ለታዳሽ ሀይል የሚመደቡ በጀትን ማሳደግና እንዲሁም የመንግስትና የግል አጋርነትን  በማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንዳለበት ሲያነሱ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አብርክቶ አድንቀዋል።

በታዳሽ ሀይል አቅርቦት አሁን ላይ ያልውን 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን የስራ እድል ፈጠራ በ2050 ወደ 40 ሚሊዮን  ማሳደግ ይገባልም ነው ያሉት።

ዘርፉን ለማበረታታትም ሀገራት የፖሊሲ ማሻሻያዎች በታክስ ቅነሳ ፤በድጎማ፣ በዋስትና እና  በጥናቶች መደገፍ እንደሚገባቸው መናገራቸውን  ከውሀና  ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም