የፌዴራሊዝም ጥናት ባለሙያዎች ማህበር ተመሰረተ

208

አዳማ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በፌዴራሊዝም ላይ ጥናትና ምርምር  የሚያደርግ የፌዴራሊዝም ጥናት ባለሙያዎች ማህበር  ዛሬ ተመስርቷል።

ማህበሩ የተመሰረተው የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ ያዘጋጁትን የውይይት መድረክ ሲያጠናቅቁ ነው።

በማህበሩ የተመረጡት ሰባት አባላት ያሉት መስራች የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማህበሩን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችን በመምረጥ ለጠቅላላ ጉባኤው እንደሚያቀርብም ተገልጿል።

የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ እንደገለፁት፤ ማህበሩ በፌዴራሊዝም ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለመንግስት ምክረ ሀሳብ ማቅረብን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ተቋቁሟል።

የማህበሩ አባላት ከሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ምሁራን መሆናቸውን ገልጸው፤ ሳይንሳዊ የሆነ እውቀትን ለማስተላለፍና በምርምር ግኝቶች መፍትሔ ለመጠቆም የሚያስችል አቅም እንዳላቸው አክለዋል፡፡

ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራሊዝም ክበብን በማቋቋም ወጣቶችን በማሰልጠን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡


 

በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም ጥናት መምህር አዳሙ ጅባት በፌዴራሊዝም አስተምህሮ ላይ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራ ማህበር መዋቀሩ በዘርፉ ያለውን ብዥታ ለማጥራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።፡

ማህበሩ የፌዴራሊዝም አረዳድ ያላቸው አመራር አባላትን በመፍጠር የመንግሥትን አቅም ለመገንባት ድርሻ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

የባለሙያውን አቅም በተደራጀ የአሰራር መዋቅር በማጠናከር ፀረ ህብረ ብሔራዊ አመለካከቶችን ለማስተካከል አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርስቲያቸው ወጣቶችን በማራጀት የፌዴራሊዝምን አስተሳሰብ የሚያራምድ ትውልድ ለመገንባት ጥረት እንደሚያደርጉም መምህር አዳሙ አስታውቀዋል፡፡


 

በአምቦ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም ጥናት መምህር ሰለሞን ተፈራ ''ማህበሩ በሚያከናውናቸው ጥናቶችና ምርምሮች ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቋሚ ሃሳብ በማቅረብ የአገረ መንግስት ግንባታውን ለማረጋገጥ ይሰራል'' ብለዋል፡፡

እንደ የአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ ፌዴራሊዝም ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ ለማህበራዊ እንዲሁም ለማንነትና ሰላም ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱን በቀጥታ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በዩኒቨርሲቲዎች የፌዴራሊዝም ክበብን በማቋቋም ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ሊገነባ  የሚችል ትውልድን ከመሠረቱ ለማነፅ እንደሚያስችልም እምነታቸውን  ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም