ቀጥታ፡

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላችንን ተሳትፎ እያደረግን ነው -የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በአዋጅ ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡

ኮሚሽኑ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ በማድረግ የተረጋጋች አገር ለመገንባት ትልቅ እምነት ተጥሎበታል፡፡

በምክክር ሒደቱም አሳታፊ እንዲሆን ከወዲሁ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችም ለምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጅ ኢብራሔም ቱፋ፤ የአገራዊ ምክክሩ ዓላማ ልዩነቶችን በውይይትና ምክክር መፍታት መሆኑን በሚገባ እንገነዘባለን ነው ያሉት፡፡

ህብረተሰቡ ስለ ምክክሩ አስፈላጊነት በማስገንዘብ ለውጤታማነቱ እንዲተባበር የበኩላቸውን ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያነሱት፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሊቀ-አእላፍ ቀሲስ እያሱ ናሁሰናይ በበኩላቸው፤ ለአገር ሰላም ለሚሰሩ ሁሉ ድጋፍ እና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

"ሁሉም እምነት ለሰላም ቅርብ ነው፣ ሰላምን በጽኑ ይፈልጋል"  ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ሁላችንም ለሰላም በሰላም ተጋግዘንና ተረዳድተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ፤ ስለ ሰላም ለምዕመኖቻችን ማስተማር መምከርና ምሳሌ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


 

"እኛ የሃይማኖት ሰዎች ለየትኛውም ወገን ሳንወግን ስለ ሰላም የሁሉም አባት መሆናችንን በተግባር ማሳየት አለብን" ብለዋል፡፡ 

የምክክሩን ዓላማ በሚገባ እናውቃለን ስለዚህ ለስኬታማነቱ የበኩላችን አስተዋጽኦ እናበረክታለን ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ስራውን ለመስራት ሰላም ያስፈልጋል፤ ሰላም እንዲሰፍን ምእመኖቻችንን በማስተማር የበኩላችንን እየተወጣን ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ናቸው፡፡


 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩ ይታወሳል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም