ኮሚሽኑ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈቃድ የሰጣቸው ኩባንያዎች ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲገቡ ክትትልና ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

95

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈቃድ የሰጣቸው ኩባንያዎች ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲገቡ የሚያደርገውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያጠናክር የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን አሳሰበ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራና ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የተወጣጣ የሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሟል።  

ቡድኑ ከፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የስራ ስምሪት ተቀብሎ የተለያዩ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ እየተመለከተ ሲሆን በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ተቋማዊ እንቅስቃሴ ቃኝቷል።

የኮሚሽኑ የስራ ኅላፊዎች ለሱፐርቪዥን ቡድኑ ባቀረቡት ገለጻ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የተጣጣሙ ዕቅዶችን አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ነው።

ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣  የፕሮሞሽን እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ተግባራትን በማከናወን ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።

ከሰሞኑ የፀደቁ መመሪዎችን ጨምሮ አዳዲስ ኢንቨስትመንት መሳብ እና በስራ ላይ የተሰማሩትን የበለጠ የሚያተጉ የሕግ ማዕቀፎችን የመተግበር እርምጃዎች መወሰዳቸውንም እንዲሁ።

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኢንቨስትመንት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ዲጂታል ስርዓት ለመዘርጋት በሂደት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት 9 ወራት 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለ ሲሆን በኢንቨስትመንት ፈቃድና ክትትል ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ 248 አዳዲስ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል 170ዎቹ በሙሉ የውጭ ኩባንያዎች፣ 48ቱ የሀገር ውስጥና የውጭ እንዲሁም ቀሪዎቹ የሀገር ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።

የአስፈፃሚ ተቋማት ቅንጅት ጉድለትና ብቃት ማነስ፣ የመሰረተ ልማትና ግብዓቶች አቅርቦት እጥረት፣ የፖሊሲና ሕግ ክፍተቶች አሁንም የዘርፉ ችግሮች እንደሆኑ ተነስቷል።

የሱፐርቪዥን በድኑ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት የሱፐርቪዥን በድኑ ክትትልና ግምገማ የተቋማት አበረታች ስራዎች እውቅና እንዲቸራቸውና ክፍተቶች እንዲታረሙ ለማድረግ ያግዛል።


 

የተቋማት ዕቅዶች ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተጣጥመው መተግበር እንዳለባቸው ገልጸው፤ ኮሚሽኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አኳያ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አኳያ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ፈተናዎችን ተቋቁሞ  ከባለፈው ዓመት  ጋር ተቀራራቢ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማበረታቻ የሚደረገው ኢንቨስትመንቶቹ ለሀገር ኢኮኖሚያ ዕድገት እና ስራ እድል ፈጠራ ካላቸው ሚና አንጻር ተመዝነው ውጤታማነታቸውም ተረጋግጦ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ ባለፈ ፈቃድ የሰጣቸው ኩባንያዎች ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲገቡ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ኢንቨስትመንት ወደ ተግባር እንዲለወጥና በሂደትም ወደ ላቀ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገር ለማስቻል የሚሰጡ ማበረታቻዎች በትክክል ገቢራዊ ስለመደረጋቸው ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ የሚሰሩ ተቋማት ተወካዮች እንደተካተቱበት ገልጸው ግምገማው የዘርፉ ተግዳሮቶች በቅንጅት እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ስራዎች ውጤታማነት የሚለካው ከሌሎች የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በሚሰራው የተቀናጀና የተናበበ ስራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ረገድ ከተቋማት ጋር ያለው ትስስርና የተናበበ አሰራር መጠናከር አለበት ብለዋል።

በሱፐርቪዥን ቡድኑ ግምገማ የተለዩ ጉዳዮችን ያካተተ ሪፖርት የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ክፍተቶች እንዲታረሙ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ በዕለቱ ከሱቨርቪዥን በድኑ ጋር የተደረገው ውይይት በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለማረም የሚያስችል ፍሬያማ እንደነበር ተናግረዋል።


 

ኮሚሽኑ በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ ምቹ ኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠር ኢንቨስተሮችን በመሳብ ሀገርን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ማነቆዎችን የመፍታትና ቆይታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በቅርቡ የጸደቀው የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው መመሪያ ሸማቹ ህብረተሰብ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚያስችለው ጠቁመዋል።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ በተመረጡና ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች የሚያደርገው የመስክ ምልከታ እስከ ሚያዝያ 24 / 2016 የሚቀጥል ይሆናል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም