ሁሉም ዜጋ ደም መለገስን ባህል በማድረግ ሰብዓዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል-   በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች

58

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ ሁሉም ዜጋ ደም መለገስን ባህል በማድረግ  በደም እጥረት ምክንያት የዜጎች ሕይወት እንዳያልፍ ሰብዓዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ገለጹ።

የባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት ሰራተኞቹን እና ድርጅቱ በሚገኝበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን በማስተባበር የደም ልገሳ መርሐ ግብር አከናውኗል።

የደም ልገሳው ዓላማም በደም እጥረት ምክንያት ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ መታደግን እንደሆነ ተገልጿል።

የድርጅቱ መስራችና ዳይሬክተር ሀናን ሙሐመድ እንዳሉት ድርጅቱ ሰራተኞችንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር የደም ልገሳ ሲካሄድ የዛሬው ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

በመርሐ ግብሩ 200 በጎ ፈቃደኞች ደማቸውን እንደለገሱ ጠቁመዋል።

ደም መለገስ የመልካምነትና የበጎነት መገለጫ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ በደም እጥረት ምክንያት የሰው ሕይወትን እንዳያልፍ ሁሉም ዜጋ ደም መለገስ ባህል ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

ለሰባተኛ ጊዜ ደም መለገሱን የሚገልጸው ሳላዲን ከድር ደም መለገስ የሰውን ሕይወት በመታደግ ደስታ ከመፍጠር ባለፈም የመልካምነት መገለጫ ተግባር ነው ብሏል።

ወይዘሮ  ፀሐይ ስንታየሁ በበኩላቸው ደም መለገስ ሕይወትን ማትረፍ መሆኑን በመገንዘብ ዜጎች በዘላቂነት በዚህ በጎ ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት በበጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በ2012 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የተቋቋመ ሲሆን ለአቅመ ደካማ ወገኖች የምገባ አገልግሎትን ይሰጣል።

ድርጅቱ ከምገባ አገልግሎቱ ባሻገር የደም ልገሳ፣የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን ያከናውናል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም