በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሳካት በሚከናወኑ ተግባራት የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች

153

ወልቂጤ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የለውጡን ስኬቶች በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሳካት በሚከናወኑ ተግባራት የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

ዛሬ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ህዝባዊ መድረክ ተካሂዷል።


 

በሕዝባዊ መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህዝባዊ መድረኩ ተሳታፊዎችም ለጠቅላይ ሚኒስትሩና በለውጡ ለተገኙ የልማት ስኬቶች ያላቸውን ድጋፍና አድናቆት ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ አገራዊ ለውጡን በማጽናት የተጀመረው ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ከግብ እንዲደርስ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

ከተሳታፊዎች መካከል የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መችበዙ ገብሬ፤ በአገራዊ ለውጡ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች በመከናወናቸው የተገኙትን ውጤቶች ለማስቀጠል የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አስታውሰው፣ በአገራዊ ለውጡ የተገኙ ስኬቶችን ለማድነቅና ለመደገፍ ወደ ሕዝባዊ መድረኩ መምጣታቸውን ተናግረዋል። 

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ባለፉት ጊዜያት በአካባቢያቸው ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ልማት እንዲጓተት አድርጓል።  

ይሁን እንጂ መንግስት ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ በመነጋገሩና በመስራቱ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ጠቅሰው፣ "የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ከመንግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን" ብለዋል።

"ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን መመሪያ ተቀብለን ሰላምና አብሮነትን በማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ  ለውጥ ለማምጣት እንተጋለን" ሲሉም ገልጸዋል። 

ከእንደገኝ ወረዳ የመጡት አቶ ሙሉጌታ ገብሬ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) በአካባቢው ተገኝተው ከህዝቡ ጋር በመነጋገራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል ። 

አካባቢያችን ሲለማ ተጠቃሚ የምንሆነው እኛው ስለሆንን ሁላችንም ለሰላምና ለልማታችን የሚጠበቅብንን መወጣት አለብን፤ ለእዚህም ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ውጥኖችን መደገፍ ለተተኪው ትውልድ የበለፀገች አገር በጋራ ለማቆየት ወሳኝ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ አክለዋል።

ለእዚህም የሰላም ዋጋ የማይተካ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላምና ልማት ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የለውጡ መንግስት ሁሉን ያሳተፈ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ያለው ደግሞ ከጉመር ወረዳ መምጣቱን የገለጸው ወጣት ሱለይማን በድሩ ነው።

በአሁኑ ወቅት እንደአገር በቱሪዝም፣ በግብርናና በሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የሚደገፉና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን ተናግሯል።

በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አገርን ከፍ የሚያደርጉ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ሱለይማን፤ የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የሁሉም ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም