የሚገጥሙን ፈተናዎች ሳያቆሙን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የጀመርናቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን

157

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦የሚገጥሙን ፈተናዎች ሳያቆሙን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የጀመርናቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የለውጡን መንግስት የሚደግፍ ሕዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጉራጌ ጎጎት በተባለው ቃል ኪዳኑ ስለ አንድነትና አብሮነት አበክሮ ያስተማረና በተግባር የኖረ ማህበረሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለማጋጨት በየዕለቱ ብዙ ለሚጥሩ ጠላቶች ሁሉ መላው ኢትዮጵያዊ የአንድነትን ኃያልነት በመማር ይችን ድንቅ ሀገር ለልጆቹ አበልፅጎ ለማስረከብ እንዲሰራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጉራጌ ስለ ሰላም የሚያስተምርና በሰላም የሚኖር ምሳሌ የሆነ ህዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለሰላም ሳናስብ እና ሳንኖር ሰላምን ማግኘት አይቻልም ብለዋል።

መላው ኢትዮጵያን ሰላምን አብዝቶ መፈለግ፣ በአብሮነት በመኖር የበለፀገችና ለሁሉ የምትመች ኢትዮጵያን ለማየት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል። 

ኢትዮጵያውያን ብዙ የማንነት መገለጫ እንዳለን በመቀበል፣ የባሀል፣ የቋንቋ፣ የአካባቢ አቀማመጥ ልዩነት ኢትዮጵያ ጥንካሬ መሰረት ሊሆን እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የጉራጌ ህዝብ  በውስጡ የተለያዩ ማንነቶች ቢኖሩትም በጉራጌነት አንድ ሆኖ በመኖር የኢትዮጵያ አንድነት ምሳሌና ምልክት ሆኖ መኖሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለነጻነቷ የተጋደለችና ያልተገዛች ሀገር ብትሆንም ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት በመላቀቅ ነጻነቷን ምልዑ ለማድረግ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያን በብርቱ ጥረት ወደ ብልፅግና ከፍታ በመውሰድ የአፍሪካ የነጻነትና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መትጋትን መርጠናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለዚህ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ታታሪው የጉራጌ ህዝብ ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ ትበለፅጋለች የሚል ፅኑ አቋም ይዞ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባም አንስተዋል።

የተሟላ ሰላምን መጎናፀፍ የሚቻለው ስለ ሰላም በማሰብ፣ በመኖር እና ሰላምን በማስተማር መሆኑንም መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል።

"በዚህ ሰዓት በጫካ እና በአንዳንድ ስፍራ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ከላኳችሁ እና ከሚከፍሏችሁ  ኃይሎች ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጣለች" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ኃይሎች ከከፋፋይነት፣ ከሰፈርተኝነት፣ ከመንደር እሳቤ ወደ አብሮነትና ኢትዮጵያዊነት እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትበለፅገው በብርቱ ጥረት መሆኑን ገልፀው፤ ሀገርን ለመከፋፈልና ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎችን ቅዠት ለማክሸፍ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሚገጥሙን ፈተናዎች ሳያቆሙን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የጀመርናቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም