የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በመደመር ዕሳቤ በአዲስ ጉልበትና ምዕራፍ መትጋት ይገባናል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው 

143

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በመደመር ዕሳቤ በአዲስ ጉልበትና ምዕራፍ መትጋት ይገባናል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ተናገሩ።

የለውጡን መንግስት ለመደገፍ ያለመ ህዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የማዕከላዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በሀገር ግንባታ ሂደት የጉራጌ ማህበረሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ዴሞክራሲያዊ ስርአት ባልነበረበት ጊዜም ጭምር በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንባታ ጉልህ አበርክቶ እንደነበረው ተናግረዋል።

ከስድስት ዓመታት በፊት ለውጥ እንዲወለድ በማድረግ ረገድም ከለውጥ ፈላጊ አካላት ጋር በመሆን ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

በለውጡ ማግስትም ራሱን ችሎ በክልል ለመደራጀት መንቀሳቀሱንና በኋላም በተደረጉ ውይይቶች የክላስተር አደረጃጀትን መርጦ ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር መደራጀቱን አስታውሰዋል።

በዚህም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተመስርቶ በአዲስ ጉልበት በአዲስ ምዕራፍ ለለውጥ እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬም በዘመነ መደመር ከለውጡ መንግስት ጎን በመቆም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስር እንዲሰዱ ለማድረግ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል። 

የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግም ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል ነው ያሉት። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጉዞ የጉራጌ ማህበረሰብ እንደሚደግፍም ነው የተናገሩት።

የትጋትና የልማት ተምሳሌት የሆነው የጉራጌ ማህበረሰብ የለውጡን መሪና መንግስት በመደገፍ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ይተጋል ብለዋል።

ህዝቡ በቀጣይም የተጀመሩ ልማቶችን በማጠናከር አገራዊ ብልጽግናን እውን የማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የጉራጌ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እንደ ስንቅ ይዞ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተሰማርቶ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመደመር ዕሳቤን የተረዳና እየተገበረ የሚገኝ ማህበረሰብ መሆኑን ገልጸው በመረዳዳት መንፈስ ሁል ጊዜ ለለውጥ የሚተጋ ነው ብለዋል።

ስራ ሳይንቅ በመስራት የይቻላልን መንፈስ በተግባር ያስተማረ ማህበረሰብ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ አገራዊ ለውጡ እንዲወለድ ከለውጥ ፈላጊ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ዋጋ መክፈሉን ገልጸዋል።

አሁን ደግሞ ለውጡን በማጽናትና ብልጽግናን በማረጋገጥ ረገድ በበለጠ ትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም