በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አዲስ አምራች ኩባንያ ተመርቆ ስራ ጀመረ 

71

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባቲ ትሬዲንግ የተሰኘ ኩባንያ የማምረቻ ሼድ ውስጥ ማምረቻ ማሽነሪዎችን በመትከልና በመገጣጠም በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀምሯል። 


በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሀመድ አሚን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ኩባንያውን በይፋ ስራ አስጀምረዋል። 

በስራ ማስጀመሪያ ስነስርአቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ባቲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽኑ አቅም ላላቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎች የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።



 
ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም አሁንም አቅም ያላቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ ያደረገውን ያጠረ የቢሮክራሲ አሰራር እና ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎችን በመጠቀም ወደ ኢንቨስትመንት እንዲመጡ ጋብዘዋል።

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ስራ የጀመረው ባቲ ትሬዲንግ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ ጥጥን በግብዓትነት በመጠቀም ክር የሚያመርት መሆኑም ተመላክቷል። 


 

ኩባንያው አሁን ላይ 300 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ምርቶቹንም ሙሉ ለሙሉ ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሪን በማዳን በኩል ሚና እንደሚኖረው መገለጹን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም