በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ባለሃብቶችን በመደገፍ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ማነቃቃት ይገባል --አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

64

ደሴ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ከማድረግ ባሻገር የግል ባለሃብቶችን በመደገፍ ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት በተሻለ ቅንጅት መስራት እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት ዋና  አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

''የኢትዮጵያ ታምርት''  የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።


 

አፈ-ጉባኤዋ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ክልሉ ያለው ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሌሎች እምቅ ሃብቶች ለኢንቨስትመንት ምቹ ናቸው።

ይህንኑ ሃብት በአግባቡ በማልማት የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በቅንጅት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የክልሉን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር የግል ባለሃብቱን በመደገፍ የኢንቨስትመንት ዘርፉን የበለጠ የማነቃቃት ስራ መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይ የዘርፉን ተግዳሮቶች በመፍታት ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት ከማምረት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጡ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፤ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በቅንጅት በመፍታት ዘርፉን የማነቃቃት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይ የክልሉ መንግስት በከፍተኛ ወጪ የመሰረት ልማት ችግሮችን እያቃለለ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ክፍተቶችን በማረም ተኪ ምርት እንዲያመርቱ የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህም 241 አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ 38 ቶን ተኪ ምርት መመረቱን ጠቅሰው፤ በተመረተው ምርትም ለውጭ ምንዛሬ ይወጣ የነበረን 195 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን ገልፀዋል።

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 276 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 885 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት ዘርፉን የማገዝ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን የማነቃቃቱ ተግባር ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሃመድ አሚን የሱፍ ናቸው።

በከተማው ለሚገኙ 58 መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ በማድረግ 28 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርት ለማምረት መቻላቸውን ገልፀው ምርቱን ወደ ውጪ በመላክም 36 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አብራርተዋል።

የሪሀመር ፒቢሲና ቀለም ፋብሪካ ተወካይ አቶ ጀማል ታደሰ፤ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት መሰረት በማድረግ በ114 ሚሊዮን ብር ካፒታል በኮምቦልቻ ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

የዝገትና የብረት ቀለም፣ የተለያዩ የውሃ ማስተላለፊያ የፕላስቲክ ቱቦዎችን እና ሌሎችንም በማምረት ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎችን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም