የዞኑ አርሶ አደሮች ደጋግሞ የማረስ ስነ ዘዴን በመጠቀም የእርሻ ማሳቸውን ለቀጣይ መኸር እያዘጋጁ ነው

74

ደብረ ማርቆስ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ለ2016/17 ዓ.ም የምርት ወቅት የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ደጋግሞ የማረስ የግብርና ስነ ዘዴን በመጠቀም ማሳቸውን ለዘር ስራ እያዘጋጁ መሆናቸውን ገለፁ።

ለቀጣዩ የመኽር ሰብል ልማት ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በድግግሞሽ ታርሶ ለዘር ስራ መዘጋጀቱም ተገልጿል።

የጎዛምን ወረዳ የሊባኖስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የቆየ ታምራት እንዳሉት፤ ለመጪው የመኸር ሰብል ልማት ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ለዘር ስራ አዘጋጅተዋል።

ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎችም ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ በመግዛት የዝናቡን መጣል እየተጠባበቁ እንደሆነም ተናግረዋል።

የዚሁ ወረዳ የየቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዳግም አራጋው እንዳሉት፤ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚለማውን መሬት ከወዲሁ ደጋግመው እያረሱ ይገኛል።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ ሦስት ሄክታር መሬት እስከ ሦስት ጊዜ ደጋግመው ማረስ የቻሉ ሲሆን ከታረሰው መሬት ሩብ ሄክታር በሚሆነው ላይ ድንች መዝራታቸውን ተናግረዋል።

ለመኸር ሰብል ልማቱ የሚውል ማዳበሪያ ከወዲሁ በበቂ መጠን እየቀረበ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም ባለፈው ዓመት ከማዳበሪያ ጋር ተያይዞ ገጥሟቸው የነበረው ችግር በመፈታቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢያለ አለኸኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አርሶ አደሩ ለ2016/17 የምርት ዘመን የሚውል የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ እያከናወነ ይገኛል።

በመጪው የመኸር ወቅት ከ612 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁን በተደረገ ጥረት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዙር ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ለዘር ስራ ተዘጋጅቷል።

ከታረሰው መሬት ውስጥም ከሦስት ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በትራክተር የታረሰ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚሁ የመኸር እርሻ ዝግጅት ከ260 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ "ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሴት አርሶ አደሮች ናቸው" ብለዋል።

በመኸር ወቅት በዞኑ ከሚለማው መሬትም ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ተመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም