በጋምቤላ ክልል የአካባቢ ብክለት በሰውና በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በጋራ መስራት ይገባል-- -ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ

ጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የአካባቢ ብክለት በሰውና በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የክልሉ ሕዝብ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ። 

"ብክለት ይብቃ! ውበት ይንቃ!" በሚል መሪ ሀሳብ ለስድስት ወራት የሚተገበር የአካባቢ ብክለትን የመከላከል የንቅናቄ መርሃ ግብር በክልል ደረጃ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የአካባቢ ብክለት ችግሮችን ለመፍታት የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቶችን ማዘመን ያስፈልጋል። 

በክልሉ የአካባቢ ብክለት ችግሮች በሰው ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል። 

የአካባቢ ብክለት  በአየር፣ በውሃ፣ በአፈርና በሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለውን  ጉዳት ለመከላከል ኅብረተሰቡን በማሳተፍ  እንዲሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በተለይም የፕላስቲክ ብክለት የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ምርቶቹን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

ለንቅናቄው ውጤታማነት የክልሉ ህዝብ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ተወካይ አቶ ሺፈራው ነጋሽ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የፕላስቲክ ቆሻሻ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።

በተጨማሪም የፕላሰቲክ ቆሻሻ በየብስና በውሃማ አካላት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት ለአካባቢ ውበትና ለብዝሃ ህይውት መመናመን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የፕላስቲክ አጠቃቀምና አወጋገድ ስርዓቱን በማዘመን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት እንዲሰራ ጠይቀዋል።  

የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጄት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በንቅናቄው የክልሉ ሕዝብ በአካባቢ ብክለት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን  አስታውቀዋል። 

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአካባቢ ብክለት ንቅናቄ በሰዎችና በእንስሳት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስና ለማስቀረት አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም