መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ላይ ግንዛቤን ለመፍጠር የተጠናከረ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል-የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

149

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ፋይዳን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር  በትኩረት እንዲሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአገራዊ ምክክርና ሽግግር ፍትህ ለሰብአዊ መብት መከበርና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትልቅ ፋይዳ አላቸው።

በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተፈጠሩ ስብራቶችን በመጠገንና አብሮነትን በማጠናከር ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያለውን ፋይዳ አንስተዋል።

በምክክሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አጀንዳውን ይዞ በሰለጠነ መንገድ በመወያየት ለአገር የሚበጀውን ሀሳብ የጋራ ለማድረግም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ ቀደም ሲል የተፈጠሩ ችግሮችን፣ ለማረም፣ እውነትን ለማውጣት፣ ለተጣሱ ሰብአዊ መብቶች ፍትህ በመስጠት ወደፊት ለመሄድ የአገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ ትልቅ መፍትሄ እንዳለው ተናግረዋል።

ስለዚህም ህብረተሰቡ ስለ  የአገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በአግባቡ ተረድቶ የታለመለትን ዓላማ ግብ እስኪመታ እንዲያገዙ መገናኛ ብዙሃን ግንዘቤ መፍጠር ላይ አበክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡ ግልጽ አረዳድ እንዲኖረው፣ አወንታዊ ምልከታ እንዲፈጠር፣ ሂደቱን ከሚያደናቅፉ ዘገባዎች በመቆጠብ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃን የአዘጋገብ ስነ-ምግባር ላይ ተመስርቶ እንዲዘግቡ የሚሰጠውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።   

የአገራዊ ምክክርና ሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ቀጣይ የአገርን እጣ ፋንታ የሚወስኑና ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያላቸው በመሆናቸው መገናኛ ብዙሃን በበጎ ምልከታ ሊዘግቡ ይገባል።

ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር በባለቤትነት እንዲሳተፍ፣ የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱና ሃሰተኛ መረጃዎችን በመመከት መስራት ይግባል ሲሉም አክለዋል።

በኢትዮጵያ አላግባባ ያሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባትና ለተጣሱ ሰብአዊ መብቶች ፍትህ ለመስጠት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም