በተፈጠረልን የስራ እድል ከራሳችን አልፈን አካባቢያችንን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረናል

73

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በተፈጠረልን የስራ እድል ከራሳችን አልፈን አካባቢያችንን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረናል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ  የሚገኙና በማህበር የተደራጁ ዜጎች ገለጹ።  

ከመገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ ባለሙያዎች በሸገር ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም በሸገር ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ115ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩ ተጠቁሟል።

በሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች መንግስት በፈጠራቸው የስራ ዕድል በመጠቀም ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸው በመትረፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መሃሙድ አህመድ እና ፉአድ አብደላ ለበርካታ ዓመታት የስራ ዕድል ባለማግኘታቸው ቤት ሲቀመጡ እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን ላይ በማህበር ተደራጅተው በዶሮ እርባታ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው፤  ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በማህበራቸው ከ2 ሺህ በላይ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በመግዛት መንከባከብ መጀመራቸውን ጠቁመው ከሁለት ሳምንት በኋላ በቀን ከ2ሺህ በላይ እንቁላል የማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በመንግሥት በኩል የቦታ አቅርቦትን ጨምሮ የብድር እና አስፈላጊ የተባሉ ድጋፎች እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል።

በዚሁ ክፍለ ከተማ በወተት ላሞች እና በሰንጋ ማደለብ ስራ ላይ የተሰማሩት አብዱረህማን ከድር እና ሰሚራ አብዱረህማን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በቀን ከአንድ መቶ  ሊትር በላይ ወተት  በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ይህን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ለመጪው የፋሲካ በዓል ያደለቧቸውን በሬዎችን ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወጣት ፍቃዱ ሸንተማ በበኩሉ በማህበር ተደራጅተው 40 ሰንጋዎችን በማደለብ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ሃይሉ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በተለያዩ ዘርፎች ከ9 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የሸገር ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሃይሉ ደራርሳ በበኩላቸው ፤ የሸገር ከተማ አስተዳደር አመቺ የስራ ዕድል በመፍጠር ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ115 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል።

በ7ሺህ 265 ማህበራት የተደራጁ ወጣቶች የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው ለነዚህም ከስልጠና ጀምሮ የመስሪያ ቦታ መመቻቸቱንም ተናግረዋል።

የስራ ዕድሉ በተለያዩ ዘርፎች መፈጠሩን የገለጹት ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊው የማኑፋክቸሪንግ፣ የግንባታ፣ የእንስሳት እርባታ፣ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታ እና የንግድ ዘርፍ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

የከተማ አስተዳደሩ አስር ኢንሼቲቮችን በመለየት ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመስራት ላይ እንደሚገኝ በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም