ዜጎች በሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም ዙሪያ የጋራ አረዳድ እንዲኖራቸው ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

146

አዳማ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ ዜጎች በሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም ዙሪያ የጋራ አረዳድ እንዲኖራቸው ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ጠየቀ።

በአዳማ ከተማ የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር በፌዴራሊዝም ስርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዷል።


 

የሕገ-መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለእየሱስ ታዬ፣  ዜጎች በፌዴራሊዝም ዙሪያ የጋራ አረዳድ እንዲኖራቸው ምሁራን ሀሳቡን የማስረፅ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የፌዴራሊዝም ስርዓትን በተሟላ መልኩ ለመተግበር ማህበረሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ እውቅት መጨበጥ እንዳለበትም አንስተዋል።

በዚህም የህገ መንግስትና የፌዴራሊዝም ስርዓት አረዳዱ የዳበረና ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያደርግ ማህበረሰብ ለመገንባት ምሁራን ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ውድሻ በበኩላቸው በፌዴራሊዝም አረዳድ ላይ እየታዩ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከዘርፉ ምሁራን  ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

እንደ አገር ወደፊት የሚያራምድ ስርዓት ለመገንባት ከምሁራን ባሻገር የተሻለ ግንዛቤ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ሀሳቡን ለማስረጽ መትጋት አለበት ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ያዕቆብ በቀለ፣ በስርዓቱ ዙሪያ የተሟላ አረዳድ ባለመፈጠሩ የአፈፃፀም ሂደቱ ላይ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን አንስተዋል።

''ዋና ትኩረት መሆን ያለበት የእውቀት ማጎልበት ስራውን በማጠናከር የህዝብ አስተዳደሩን ለህዝብ ተደራሽና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ አቅም መፍጠር ነው'' ብለዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ የማነህ ወልዴ፣ ፌዴራሊዝምን የማስገንዘብ ስራ ውስጥ ምሁራን ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

በቀጣይም የዘርፉን ምሁራን አቅም በመጠቀም በሁሉም ደረጃ ያለውን ማህበረሰብ ለማንቃት መትጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም