ማዕከሉ የሚገኝበት ቦታ ለአገልግሎት አሰጣጥ የተመቸ አለመሆን ለእንግልት ዳርጎናል- ቡና ላኪና አቅራቢዎች

76

ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦  የሀዋሳ የምርት ጥራትና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል የሚገኝበት ቦታ ለአገልግሎት አሰጣጥ የተመቸ አለመሆን ለእንግልት እየዳረገን ነው ሲሉ  የቡና ላኪና አቅራቢ ተወካዮች ቅሬታቸውን ገለጹ ።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ማዕከሉ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በ2015 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ በይፋ ስራ የጀመረው ማዕከሉ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከሲዳማ ክልሎች ለሚመጣው  የቡና ምርት የጥራት ደረጃ እየሰጠ ወደ ኤክስፖርት ማዘጋጃ የመላክ ተግባር ያከናውናል።

ይሁን እንጂ ማዕከሉ የሚገኝበት ቦታ ለአገልግሎት አሰጣጥ የተመቸ አለመሆን የጥራት ደረጃ የመስጠት ሂደቱ ቀልጣፋ እንዳይሆን በማድረግ ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረገን ነው ሲሉ  የቡና ላኪና አቅራቢ ተወካዮች ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ለኢዜአ ቅሬታቸውን ካቀረቡት መካከል የቡና አቅራቢና ላኪ ተወካይና ባለቤት አቶ ታደሰ ደባልቄ የማዕከሉ አዲስ መሆንና ቡና የጫነ መኪና ማቆሚያ አለመኖር ለአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ዳርጎናል ብለዋል።

በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቡና የጫነ መኪና መንገድ ዳር በማቆም ወረፋ እንድንጠብቅ ተገደናል ሲሉም ገልፀዋል።


 

የማዕከሉ ሃዋሳ ላይ መከፈት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም የተመረጠው ቦታ ግን የስራውን ባህሪ ያገናዘበ አይደለም ያሉት ደግሞ ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ረሺድ ራህመቶ ናቸው ።

ቢሮው ጠባብና የተደራጀበት መንገድ አመቺ አለመሆን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳናገኝ ምክንያት ሆኗልና መፍትሄን እንሻለን ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሃዋሳ ምርት ጥራትና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሲማ የተነሳው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው ማዕከሉ ሲከፈት በጊዜያዊነት መከፈቱን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት የቢሮ ጥበት መኖሩን ጠቅሰው ለተገልጋዮች ተገቢና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ለሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማዕከሉ ሀዋሳ ላይ መከፈት በክልሉ ያለው ከፍተኛ የቡና ምርት በጥራት ለማዕከላዊ ገበያ እንዲደርስ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ለተገልጋዮች እስከ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞና ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስቀርም ተናግረዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ ያጋጠመውን የቦታና ሌሎች ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም