በሸበዲኖ ወረዳ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት መሰረት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን እየተጎበኙ ነው

56

ሐዋሳ ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በፌዴራል የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሸን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም የተመራ ቡድን በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ፕሮግራም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን አየጎበኘ ነው።

በፕሮግራሙ በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት ባለባቸው አካባቢዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ  ይገኛሉ።

በሸበዲኖ ወረዳ በፕራግራሙ ታቅፈው በዶሮ እና ከብት እርባታ፣ የአቦካዶ ችግኝ በማፍላትና በተለያዩ የመስኖ ልማት ሥራዎች ተሰማርተው ልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ ለውጥ ያመጡ ነዋሪዎች የልማት እንቅስቃሴ በቡድኑ አባላት ተጎብኝቷል።

በመስክ ምልከታው ሚንስትሮች፣ የተለያዩ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነሮችና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

ከመስክ ምልከታው በኋላ በሀገር ደረጃ በሕጻናት ላይ የሚስተዋለውን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለመከላከል በፕሮግራሙ በተከናወኑ ሥራዎችና በመጡ ለውጦች ላይ ውይይት ይደረጋል። 

በመስክ ምልከታው የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት የተመጣጠነ ምግብ ለህጻናት በማቅረብ ጤናማና አምራች ትውልድ የመገንባት ሂደቱን ለማፋጠን የሚያስችል አቅጣጫም ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ፕሮግራም በምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር በ2022 ከሀገሪቱ ለማጥፋት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው። 

በዚህም  የመቀንጨር ችግር ባለባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የአመጋገብ ስርዓት ለማስተካከል እየተሰራ ነው።

በፕሮግራሙ በተለይ ነፍሰ-ጡር እና ወላድ እናቶች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የሥርዓተ-ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጓል። 

በተለይም አቅም የሌላቸው እናቶች ከሚፈጠርላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ በተጨማሪ ዶሮ፣ ፍየል፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በነጻ አግኝተው ወደልማት እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታ እንደተመቻቸም መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም