በዞኑ በግለሰቦች የእርሻ መሬታቸውን አላግባብ ተነጥቀው የቆዩ 800 ሴቶች ፍትህ አገኙ

84

ጎንደር ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተለያዩ ግለሰቦች የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀው የቆዩ 800 ሴቶች ይዞታቸው ተመልሶ የመብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የዞኑ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድጎ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ መሬታቸው እንዲመለስ የተደረጉት ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸውና በቅርብ ዘመዶቻቸው የእርሻ መሬታቸውን በጉልበት ተነጥቀው የቆዩ ናቸው፡፡

የሴቶችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጥረት በየደረጃው ከሚገኙ የፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ሴቶች አፋጣኝ ፍትህ አግኝተው ዳግም የመሬት ባለቤትነት መብታቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን ገልፀዋል።

ሴቶቹ ከአራት ዓመት በላይ ፍትህ አጥተው የቆዩ ሲሆን፤ መምሪያው ከህግ አካላት ጋር በመተባበር የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረጉ አሁን ላይ የእርሻ መሬታቸው ተመልሶ መጠቀም እንደቻሉም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ ከ18 ሺህ በላይ ሴት አርሶ አደሮች ደግሞ የገጠር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰርቶ እንዲሰጣቸው መምሪያው ክትትልና ድጋፍ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

በዞኑ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረትም ስምንት ሺህ ለሚጠጉ ወጣት ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

በወረዳው የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀው ፍትህ ላጡ 38 ሴቶች ከህግ አካላት ጋር በመተባበር "መብታቸው እንዲከበር ተደርጓል" ያሉት ደግሞ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት ጥጋቡ ናቸው፡፡ 

የህግ አካላት ነጻ የጥብቅና አገልግሎት በመስጠት ፍትህ ያጡ ሴቶች መብታቸው እንዲጠበቅ በማድረግ በኩል ያልተቋረጠ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 

የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ማሪቱ ጫኔ እንደገለጹት፤ በቀድሞ የትዳር አጋራቸው ተወስዶ የቆየው የእርሻ መሬት በህግ አግባብ ተመልሶላቸዋል። 

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የጭንጫዬ ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር ታክላ መንግስቴ በበኩላቸው፤ መሬታቸው ተነጥቆ ላለፉት ሶስት ዓመታት ፍትህ አጥተው ሲንከራተቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

መምሪያው ተከራካሪ ጠበቃ በማቆም ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እንዲያገኝ በማደረጉ በመሬት ሃብታቸው የመጠቀም መብታቸው እውን እንደሆነ አመልክተዋል።

በዞኑ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ40 ሺህ በላይ ሴቶች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም