በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች 747 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

ጊምቢ፤ሚያዚያ 12/2016 (ኢዜአ) በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ከ747 ሚሊዮን በላይ ምርታማና ፈጥነው  ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኖቹ ግብርና  ጽህፈት ቤቶች  አስታወቁ፡፡

የጽህፈት ቤቶቹ ሃላፊዎች ለኢዜአ እንዳስታወቁት ለተከላ እየተዘጋጁ  ያሉት ችግኞች በምርምር ምርታማነታቸው የተረጋገጡና በአጭር ጊዜ  ምርት ለመስጠት የሚችሉ ናቸው።

ዘንድሮ የሚተከሉት ችግኞች አሁን በሄክታር ከአራት ኩንታል ያልበለጠ ምርት የሚሰጡትን የቡና ዝርያዎች ምርት ወደ ዘጠኝ ኩንታል እንደሚያሳድጉት አስረድተዋል።


 

በተጨማሪም ለአራት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምርት ስለሚሰጡ፣ይህም አሁን በአርሶ አደሩ እጅ ካሉት ዝርያዎች ምርት ለመስጠት የሚያስፈልገውን ጊዜ በሦስት ዓመታት ያሳጥሩታል ብለዋል።

ችግኞቹ ከጅማ ቡና ምርምር ማዕክል የተገኙ ሲሆን፣ 'ጫላ' ፣'መና ሲቡ'፣'ሓሩ አንድ'ና 'ሲንዴ' ተብለው መሰየማቸውን ገልጸዋል፡፡

የዞኖቹ አርሶ አደሮች በግብርና ባለሙያዎች ምክርና ክትትል በመታገዝ የጉድጓድ ቁፋሮ፣ያረጁ የቡና የመንቀልና ሌሎች ለተከላ የሚያስፈልግ ዝግጅት እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም መሥፍን እንደተናገሩት በዞኑ ከ401 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።

ዘንድሮ ለተከላ የተዘጋጁት የቡና ችግኞች በነባር የቡና መሬትና በ66ሺህ በላይ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

ይህም በዞኑ በቡና የተሸፈነው 550 ሺህ ሄክታር ወደ 615ሺህ ሔክታር እንደሚያሳድገው አስታውቀዋል፡፡

የቡና ችግኞቹ በ3ሺህ 352 የግልና በ74 የመንግሥት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን የቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን ከ346 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ቡድን መሪ አቶ ታደሰ ጋሩማ አስታውቀዋል፡፡

ለተከላ እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞች በ107 የመንግሥትና በ899 የግል ችግኝ ማፍያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ 467 ሺህ 301 ሄክታር መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን አመልከተው፣ በየዓመቱም ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የሚጠጋ ምርት እንደሚሰበሰብ አስታውቀዋል፡፡

የጊምቢ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ዱጉማ ያደሳ፣ በግማሽ ሔክታር መሬታቸው ላይ የቡና ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ችግኞች ከመንግሥት ችግኝ ጣቢያ የወሰዷቸው ችግኞች በእጃቸው ካሉት የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ ከግብርና ባለሙያዎች መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ቡልቱማ ታምሩ፤ በግላቸው ከ3ሺህ በላይ የቡና ችግኞች በባለሙያ ምክር በመታገዝ እንዳዘጋጁ አመልክተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም