ባለፉት ስድስት ዓመታት 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተገንብቷል - የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር

144

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ዓመታት በመላው አገሪቱ 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተገንብቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ መንገድን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጊዜና በጥራት ከማከናወን አኳያ ጉልህ ችግር እንደነበረባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

ለህዝብ ጥቅም የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች እየተጓተቱ የምሬትና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሲሆኑም ይስተዋላል።

በተለይ በመንገድ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ ኢዜአ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ጋር ቆይታ አድርጓል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የለውጡ መንግስት በተለይ የፍጥነት የጥራት ችግሮችን በመፍታት ለህዝብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ፍትሀዊ ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። 

እስከ ለውጡ ዋዜማ ድረስ 12 ሺህ 900 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን እንደነበር አስታውሰው ባለፉት ስድስት ዓመታት በተሰራው ስራ 5 ሺህ 500 ኪሎሜትር የሚጠጋ መንገድ ተገንብቶ ህብረተሰበቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደታቻለ ገልጸዋል።

ይህም ከተደራሽነት እንዲሁም ጉዞን ከማሳጠር አንጻር ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ከ8 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆኑ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ መንገዶች ወደ ስራ ሲገቡ ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ ፍትሀዊ የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄዎችን በዘላቂነት እንደሚፈቱም ነው የገለጹት።

በግንባታ ላይ ካሉ መንገዶች ውስጥ አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም አስፋልት በጭራሽ ባልነበረባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም 9 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት የጥናት እና የዲዛይን ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ ስርጭት ከዚህ ቀደም በቂ የመንገድ ሽፋን እና በቂ የመንገድ ጥግግት ያልነበራቸው አካባቢዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገነቡ፣ በመገንባት ላይ ያሉና በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ወደ 23 ሺ ኪሎ ሜትር የሚጠጉ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ሲታዩ ሌሎች አገራት ያላቸውን የመንገድ ሽፋን የሚያህሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህም በዘርፉ ፈጣን ለውጥ የመጣበት ሁኔታን የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም