ኢትዮጵያ ባህርተኞችን አሰልጥና ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ በየዓመቱ በአማካይ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያገኘች ነው- የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን

74

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ባህርተኞችን አሰልጥና  ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ በየዓመቱ በአማካይ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያገኘች መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ከባህር ትራንስፖርትና አገልግሎት ጋር የተያያዘ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ኤጀንሲ የሆነው ዓለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት አባል አገር ናት፡፡

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1958 የተመሰረተው ዓለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት ዋነኛ ኃላፊነቱ የማሪታይም ትራንስፖርት ላይ ቁጥጥር ማድረግ ነው።

ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ 176 አባል አገራት እና 3 ተባባሪ አባል አገራት አሉት።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ማሪታይም ድርጅት አባል መሆኗ ባህርተኞችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማሰልጠን ለዓለም ገበያ አቅርባ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ እያደረጋት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬው ባህርተኞች ከደሞዛቸው ላይ ወደ አገር ቤት ከሚልኩት ገንዘብ የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ባህርተኞችን አሰልጥና ወደ ውጭ አገራት በመላክ በየዓመቱ በአማካይ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያገኘች መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ስምንት ወራት ከ36 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።

በዘርፉ ገና ያልተነካ የኢኮኖሚ አቅም መኖሩን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ከዘርፉ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ሕጋዊ እውቅና ያላቸው 7 ሺህ 500 ባህርተኞች እንዳሏት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአምስት ዓመት ይህንን አሃዝ 40 ሺህ ከፍ ለማድርግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በውጭ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ባህርተኞች በካፒቴን ደረጃ ከ1 ሺህ እስከ 20 ሺህ ዶላር እንዲሁም ዋና መሐንዲሶች እስከ 5 ሺህ ዶላር ክፍያ እንደሚያገኙም ገልጸዋል።

ባህርተኞች ልምዳቸውንና አቅማቸውን እያሳደጉ በሚሄዱበት ወቅት ከዚህም በላይ ክፍያ እያገኙ እንደሚሄዱ አመልክተዋል። 

ባህርተኞች በቢሾፍቱና ባህር ዳር ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኝና የማሰልጠኛዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ባህርተኞችን ለማሰልጠን ከመከላከያ ሚኒስቴር የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአርባ ምንጭ፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ  ዩኒቨርስቲ እና የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ባህርተኞችን እንዲያስተምሩና እንዲያሰለጥኑ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። 

በተጨማሪም ባለስልጣኑ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት ምክክር እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ልምድ እያላቸው ነገር ግን ሕጋዊ እውቅናና ተገቢው ክህሎት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በአነስተኛ ክፍያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም በአረቡ ዓለም መርከበኛ ሆነው እየሰሩ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ 

ባለስልጣኑ እነዚህ ባህርተኞች ተምረው ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ባህርተኞቹ ወደ ሕጋዊ አካሄዱ ቢመጡ በሕጋዊ መንገድ የመቀበልና ክፍያቸውን በየጊዜው የማሳደግ እድል እንደሚያገኙ ጠቅሰው ሕጋዊ የስራ ዋስትና እንደሚሰጣቸውም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን በማሪታይም ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል የማሳደግና ከአገራት ጋር በትብብር የመስራት ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም