በኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ 48 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ተደረገ

47

ነገሌ ቦረና ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፡- ከኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ 48 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ መደረጉን የዞኖቹ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች ገለጹ።

የገንዘብ አስተዋፅኦው የተሰበሰበው ከምዕራብ ጉጂ፣ ከምስራቅ ቦረናና ጉጂ ዞኖች ከህዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ወራት ከስጦታና ከቦንድ ሽያጭ ነው።

የጉጂ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሸን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ዴኮ፣ እስካሁን ከዞኑ ህዝብ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዞኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 17 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ከታቀደው በሁለት ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው 19 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

የምስራቅ ቦረና ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ጥላሁን በበኩላቸው በአምስት ወራቱ ለግድቡ ግንባታ በድጋፍ መልክ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል።

በተመሳሳይም ከምእራብ ጉጂ ዞን ህዝብ 32 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በተለያየ መልኩ ከ14 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የገለጹት የዞኑ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ባቲ ናቸው።

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍና ትብብር የዞኖቹ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንደተሳተፉም ተመልክቷል።

የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛው አቶ ተካልኝ ጃለታ፣ ለህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት እስካሁን ያልተቋረጠ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በዚህ አመት ብቻ የ8 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ የመንግስት ሰራተኛዋ ወይዘሮ ምህረት ሰለሞን በበኩላቸው የሚያደርጉት ድጋፍ የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ እንደማይቋረጥ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም