በሰሜን ወሎ ዞን በመስኖ ከለማው መሬት ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል--መምሪያው

33

 ወልዲያ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፡- በሰሜን ወሎ ዞን በአንደኛ ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ፣ መስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ አለባቸው መራዊ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርቱ የተሰበሰበው በአንደኛው ዙር በመስኖ ከለማው 17 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ነው።

በመጀመሪያው ዙር ለመሰብሰብ ከታቀደው ምርት 125 በመቶ መፈፀም መቻሉን ተናግረዋል።

ለምርት መጨመሩም የለማውን መሬት ደጋግሞ ማረስ፣ የጸረ-ተባይ መከላከል ስራ መከናወኑና 47 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እንዲሁም ማዳበሪያ በተሻለ መጠን መጠቀም በመቻሉ እንደሆነ ገልፀዋል።

በመስኖ ልማቱ ስንዴን ጨምሮ በቆሎ፣ ሽምብራ፣ ሽንኩርት እና ሌሎች አትክልቶችን ለማልማት መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚሁ ልማትም ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል።


 

የመስኖ ልማቱ የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደጉም ባሻገር ለወቅታዊ የገበያ ዋጋ ማረጋጋት ስራ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት 11 ሺ 228 ሄክታር መሬት እየለማ ሲሆን፤ 1 ሚሊዮን 254 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አቶ አለባቸው አስታውቀዋል።

በሃብሩ ወረዳ ቁጥር 13 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይማም ኑርዬ በበኩላቸው፤ በዚህ የበጋ ወቅት ካለሙት ሩብ ሄክታር መሬት  52 ኩንታል የቀይ ሽንኩርት ምርት ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።

እርሳቸው እንደገለጹት፤ ያመረቱትን ምርት በመሸጥም ከ416 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል።

በአንደኛው ዙር የመስኖ ልማት አንድ ሄክታር መሬት ስንዴ ማልማታቸውን የተናገሩት ደግሞ በራያ ቆቦ ወረዳ የ08 አራዶም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መንገሻ ዋሱ ናቸው።

ካለሙት መሬትም 31 ኩንታል ምርት ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ቀይ ሽንኩርት ማልማት መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በዚህ የበጋ ወቅት ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም