በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር እርሻ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ማዳበሪያ እየተሰራጨ ነው

37

ጎንደር ፤ ሚያዚያ 12/2016 (ኢዜአ)፡-  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅት ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ጥቅም ላይ የሚውል ከ134 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን የፀሐይ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን አስታወቀ፡፡

የዩኒየኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይሁኔ ዳኘው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ማዳበሪያው የተሰራጨው በ2016/17 የምርት ወቅት በግንቦትና ሰኔ ወራቶች ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች እንዲውል ነው።

የማዳበሪያ ሥርጭቱ በዩኒየኑ ሥር በሚገኙ 30 መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ወደ መጋዘን የገባ ተጨማሪ 10 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ወረዳዎች እየተከፋፈለ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ኮምቦልቻ መጋዘን የደረሰ 40 ሺህ ኩንታልም ወደ ዩኒየኑ መጋዘን የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ የሚውለው ማዳበሪያ 576 ሺህ ኩንታል መሆኑን ጠቁመው፤ የሚያስፈልገውን ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ በፍጥነት በማጓጓዝ የአርሶ አደሩ የዘር ወቅት ሳይስተጓጎል ለማቅረብ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦቱ በፍትሃዊነት ለማሠራጨት የሚያስችል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ናቸው።


 

ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረ የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በስርጭቱ ላይ ሕገወጥ ተግባራት መፈጸማቸውን አስታውስው፤ ዘንድሮ ይሄን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።

ግብረ ሃይሉ የማዳበሪያ ስርጭቱ ላይ ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ተከታትሎ ለህግ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ቀድመው የሚዘሩ በቆሎ፣ ዳጉሳ እና ማሽላ ሰብሎችን እንዲውል ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደምሌ ካሳ በበኩላቸው፣ በቀጣዩ ወር ቀድመው ለሚዘሩት የበቆሎ ሰብል አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። 

በሐምሌ ወር ለሚዘሩት የጤፍ ሰብል ተጨማሪ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፤ መንግስት ከወዲሁ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አበጀ አንዳርጌ በበኩላቸው፤ በመኽር ወቅት ለሚያከናውኑት የሰብል ልማት የእርሻ ዝግጅት ማድረጋቸውንና ለልማቱ የሚውል ማዳበሪያ ከወዲሁ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

በዞኑ በ2016/17 ምርት ዘመን ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም