በኢትዮጵያ የውሃ አቅሞች ወደ መስኖ ልማት ለመቀየር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ነው

503

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የውሃ አቅሞች ወደ መስኖ ልማት ለመቀየር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን የመስኖ  እና ቆላማ አካባቢ  ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስቴር ሴት ሰራተኞች በአፋር  ክልል  ገቢረሱ  ዞን የተከናወኑ የመስኖ ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

የመስኖ  እና ቆላማ አካባቢ  ሚኒስቴር  ስራ አመራር  ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ አብዱልጁሀድ መሀመድ በዚሁ ጊዜ፤  ጉብኙቱ  በሚኒስቴሩ የተከናወኑ የመስኖ ልማት ስራዎች ላይ የሴቶችን አቅም መገንባትና የጋራ መግባባት መፍጠርን ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የውሃ ሃብትን  በአግባቡ ለመጠቀምና  የምግብ  ዋስትናን  ለማረጋገጥ  ሚኒስትሩ በመስኖ ልማትና ምርምር ላይ  በትኩረት  እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡  

በኢትዮጵያ ያሉ የውሃ አቅሞችን ወደ መስኖ ልማት ለመቀየር የተከናወኑ ስራዎች በተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ  አካባቢዎችን የተመለከቱ  ፖሊሲዎችና አሰራሮችን መዘርጋት ላይ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ በአፋር ክልል የተከናወኑ የመስኖ ልማት ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የአፋር ክልል ገቢረሱ ዞን ምክትል ዋና አስተዳደሪ እና ሰላምና ጸጥታ ዘርፍ  ሃላፊ አቶ  መሃመድ ጉደሌ በበኩላቸው የአዋሽ ወንዝ በተለይ በክረምት ውቅት በዞኑ ጉዳት ሲያስከትል መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ላይ በወንዙ ላይ የተሰራው ዳይክና ተፋሰስ የጎርፍ ጉዳትን ከመቀነስ ባሻገር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ  ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በመስኖ ልማት የተገኘው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች መንግስት በዞኑ እያከነዋነው ያለው የመስኖ ልማት ሰራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳውድወሪ መሀመድ፤  አሁን ላይ በመስኖ ስንዴ ማልማት ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ  አስተያየት ሰጪ ፈጡማ ጉራታ፤ በአካባቢው ያለው የከርሰ ምድር ውሃ ጨዋማ በመሆኑ ለምርት ተቸግረው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በአዋሽ ወንዝ ላይ የተሰራው የተፋሰስ ልማት ግን አካባቢውን ምርታማ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡ 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም