አንድነታችንን በማጠናከር ሀገርን ለመከፋፈልና ህዝብን ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎችን ቅዠት ማክሸፍ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር)

87

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ አንድነታችንን በማጠናከር ሀገርን ለመከፋፈልና ህዝብን ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎችን ቅዠት ማክሸፍ ይገባል ሲሉ  ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የለውጡን መንግስት የሚደግፍ ሕዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት የጉራጌ ህዝብ ሰላምና ልማት የሚገኘው ስለ ሰላም በመስበክና በተግባር በመኖር መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

ጉራጌ በአንድነትና በአብሮነት በመኖር የሚገኘውን ጸጋ በተግባር የተገነዘበ ህዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በረጅም ዘመን ታሪኩም ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም ምሳሌ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ችግሮች ሲኖሩ በባህላዊ የምክክር፣ የሽምግልና እና የፍርድ ስርዓቶቹ በመፍታት ሰላማዊ አብሮነትን እያፀና እስከዛሬ መቀጠሉ ሊደነቅና ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ህዝብ የኢትዮጵያን አንድነት ሊንዱ ለሚፈልጉ ሃይሎች በሩን የማይከፍት እና በኢትዮጵያዊ አንድነት ፅኑ አቋም ያለው በመሆኑ ሁላችንም ለሀገራችን አንድነት መከበር በጋራ ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።

የተሟላ ሰላምን መጎናፀፍ የሚቻለው ስለ ሰላም በማሰብ፣ በመኖር እና ሰላምን በማስተማር መሆኑንም መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማናጋት የተነሱ አንዳንድ ወገኖች  ከአፍራሽ አካሄዳቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

አንድነታችንን በማጠናከር ሀገርን ለመከፋፈልና ህዝብን ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎችን  ቅዠት ማክሸፍ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለሀገራዊ አብሮነት እና አንድነት መጠናከር በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም