ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በማላቀቅ የአፍሪካ የነጻነት፣ የአንድነትና የብልፅግና ተምሳሌት እናደርጋታለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

161

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016 (ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በማላቀቅ የአፍሪካ የነጻነት፣ የአንድነትና የብልፅግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የለውጡን መንግስት የሚደግፍ ሕዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ጉራጌ ጎጎት በተባለው ቃል ኪዳኑ ስለ አንድነትና አብሮነት አበክሮ ያስተማረና በተግባር የኖረ ማህበረሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለማጋጨት በየዕለቱ ብዙ ለሚጥሩ ጠላቶች ሁሉ መላው ኢትዮጵያዊ የአንድነትን ኃይል  በመማር ይችን ድንቅ ሀገር ለልጆቹ አበልፅጎ ለማስረከብ እንዲሰራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጉራጌ ስለ ሰላም የሚያስተምርና በሰላም የሚኖር ምሳሌ የሆነ ህዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለሰላም ሳናስብ እና ሳንኖር ሰላምን ማግኘት አይቻልም ብለዋል።

መላው ኢትዮጵያን ሰላምን አብዝቶ መፈለግ፣ በአብሮነት በመኖር የበለፀገችና ለሁሉ የምትመች ኢትዮጵያን ለማየት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል። 

ኢትዮጵያውያን ብዙ የማንነት መገለጫ እንዳለን በመቀበል፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የአካባቢ አቀማመጥ ልዩነት ኢትዮጵያን የሚበትን መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል።

የጉራጌ ህዝብ  በውስጡ የተለያዩ ማንነቶች ቢኖሩትም በጉራጌነት አንድ ሆኖ በመኖር የኢትዮጵያ አንድነት ምሳሌና ምልክት ሆኖ መኖሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለነጻነቷ የተጋደለችና ያልተገዛች ሀገር ብትሆንም ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት በመላቀቅ ነጻነቷን ምልዑ ለማድረግ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ የወራሪዎችን ሙከራ የመከተችና ቅኝ ያልትገዛች ሀገር መሆኗን አውስተው፥ ሆኖም ኢኮኖሚያዊ ነጻነቷን ሳታረጋግጥ መቆየቷን አንስተዋል።

የጉራጌ ህዝብ በንግድ ዘርፍ ያሳዩት ውጤትም ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ለማላቀቅ አብነት መሆኑን አንስተው መላው ኢትዮጵያዊያን  ለልማትና ብልፅግና መቆም እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመሆኑም ከልመና ለመውጣት፣ ቁጠባን ለማዳበር፣ ንግድን ለማስፋት በአንድነት መረባበር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያን በብርቱ ጥረት ወደ ብልፅግና ከፍታ በመውሰድ የአፍሪካ የነጻነትና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መትጋትን መርጠናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለዚህ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ታታሪው የጉራጌ ህዝብ ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ ትበለፅጋለች የሚል ፅኑ አቋም ይዞ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የምትበለፅገው በብርቱ ጥረት መሆኑን ገልፀው፤ ሀገርን ለመከፋፈልና ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎችን ቅዠት ለማክሸፍ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም