ሴቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ተሰጥኦ እንዲያወጡ ሊታገዙና ሊበረታቱ  ይገባል- በስታርት አፕ አውደርዕይ የተሳተፉ ሴቶች 

172

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2016(ኢዜአ)፦ ሴቶች  በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ተሰጥኦ  እንዲያወጡና አገርን የሚጠቅም ተግባራቸውን እንዲያጎለብቱ ሊታገዙና ሊበረታቱ ይገባል ሲሉ  በስታርት አፕ አውደርዕይ የተሳተፉ ሴቶች ገለፁ።

በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ይሁን ወደፊት በእጅ የሚሰሩ ሥራዎች ቁጥርና በየቢሮው በስፋት የሚታዩ የወረቀት ብዛቶች በሙሉ በዘመናዊ፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደሚቀየሩ የሚያሳዩ ምልክቶች ብዙ ናቸው።

በአገራችንም ይህንን ታሳቢ ያደረገ የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች እየተበረታቱና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራባቸው መሆኑ በግልጽ ይታወቃል።

በአገሪቱ ያለውን እምቅ የቴክኖሎጂ አቅም ለማስተዋወቅ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።  

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ''ስታርት አፖች'' በአውደ-ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

የቢፍሮል ቲዩብ መስራች ሀይከል አህመድ በአውደርዕዩ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያግዙ ትምህርታዊ ቪዲዮዎችን የሚያቀርብ አማራጭ ይዘው እንደቀረቡ ተናግራለች።

እነዚህ ቪዲዮዎች ተማሪዎች ትምህርትን ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ በተግባር በመማር ብቁ እንዲሆኑ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅሳለች።

 አኪል የተሰኘ አገርበቀል በጎ አድራጎት ድርጅትና በጎ ፍቃደኞችን የሚያገናኝ ድረገፅ ያለማችው ቦንቱ ፉፋ  በበኩሏ ድረገፁ በጎ ፍቃደኞችንና በጎ ስራን በማገናኘት በጉልበት፣ ገንዘብና ባላቸው አቅም እንዲደግፉ የሚያስችል ነው ብላለች።

 በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የወንዶች የበላይነት ቢስተዋልም በኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ ሆነው በዘርፉ የወጡ ሴቶች መኖራቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቅሰዋል። 

ማንኛዋም ሴት እንደምትችል ካመነች ያለችውን ማድረግ ስለምትችል ስራ ላይ በማተኮር በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራት እንደምትችልም ነው የገለፁት።

መንግስት እንደዚህ አይነት አውደ ርዕይ አዘጋጅቶ የሚሰሩትን ስራ እንዲያስተዋውቁ፣ ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን አይተው እንዲበረታቱና እውቀት እንዲገበዩ በማድረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም እንደዚህ አይነት ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ማዘጋጀትና ያላቸውን እምቅ አቅም አውጥተው ለህዝብ እንዲያሳዩ የማድረጉ ስራ ሊጠናከር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ-ርዕይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።                       

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም